የባንኩ ሠራተኞች በቦረና እና ምዕራብ ጉጂ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብና የመኖ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የባንኩ ሠራተኞች በቦረና እና ምዕራብ ጉጂ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብና የመኖ ድጋፍ አደረጉ
ዲላ፤ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲላ ዲስትሪክት ሠራተኞች በቦረና እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች በተከሰተ ድርቅ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከ740 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያለው የምግብ እና የመኖ ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉን በምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደርና በቦረና ዞን ድሬ ወረዳ በመገኝት አስረክበዋል።
በባንኩ የዲላ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አላሎ እንዳሉት ድጋፉ በዲስትሪክቱ ስር የሚገኙ ሠራተኞች በራስ ተነሳሽነት ባዋጡት ከ740 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ የተደረገ ነው።
በገንዘቡም 120 ኩንታል ዱቄት፣ 450 ሌትር ዘይት እና 60 ኩንታል ፉርሽካ ተገዝቶ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ድጋፉም በሁለቱ ዞኖች በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በድርቅ ምክንያት በችግር ለተጋለጡ 480 አባውራ እና እማውራዎች የተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ባንኩ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከፋይናንስ አገልግሎቱ ጎን ለጎን ለሀገራዊ ጥሪዎች ምላሽ መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በድርቅ ምክንያት ለችግር የተዳረገውን ህዝብ ለመደገፍ መንግስትና አጋር ድርጅቶች የተቀናጀ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱሰላም ዋሪዮ ናቸው።
የባንኩ ሠራተኞች ከደመወዛቸው ከማዋጣት ባለፈ በአካል መጥተው በድርቅ የተጎዳውን ህዝብ በማየታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በቦረና ዞን የድሬ ወረዳ ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዋቆ መኩሪያ በበኩላቸው፣ በወረዳው የተከሰተው ድርቅ እንስሳትን ከመግደል ባለፈ ሰዎችን ለችግር እየዳረገ ነው ብለዋል።
ችግሩን ለመቋቋም መንግስት ከረጂ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለ42 ሺህ ህዝብ በቋሚነት፤ ለ27 ሺህ ደግሞ በጊዜያዊነት የእለት ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።
ባንኩ ያደረገው ድጋፍ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብ ድጋፍ ለማድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።