የአንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝት ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ዳግም ያነቃቃ ነው-ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝት ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ዳግም ያነቃቃ ነው-ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ
አዲስ አበባ መጋቢት 08/2015 (ኢዜአ) የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝት ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ዳግም ያነቃቃ መሆኑን ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ተናገሩ፡፡
ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የጋዜጠኝነት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም በአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ከፍተኛ አማካሪ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ብሩክ እንደሚሉት፤ 120 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ ጊዜያት መቀዛቀዞች ቢታዩበትም በአመዛኙ ግን ጥሩ የሚባል ወዳጅነት አላቸው።
ሀገራቱ ለረዥም ዓመታት በተለያዩ ሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ አብረው የሠሩ ስትራቴጂካዊ አጋሮች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአሜሪካ ኤምባሲ የከፈተች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሀገር መሆኗን ለአብነት አንስተዋል።
አሜሪካም በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መርካቶ በተለምዶ አሜሪካ ግቢ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ ቆንስላ ጀኔራል መክፈቷም እንዲሁ፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ ካላቸው የግንኙነት ታሪክ ውስጥ አብዛኛው ጥሩ የሚባል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ በኮሪያና በኮንጎ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ አብረው መሳተፋቸውን ይጠቅሳሉ።
አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ የሳተላይት ኮሙኒኬሽን ባልተዳረሰበት ወቅት በቀድሞው የኤርትራ ክፍለ ግዛት ውስጥ ቃኘው የጦር ሰፈር እንደነበራት፣ በወታደራዊና በእርሻም ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ሆኖም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዙን አስታውሰው፤ በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ጊዜ አሜሪካ በኢትዮጵያ አምባሳደር እንዳልነበራት ያወሳሉ ፕሮፌሰር ብሩክ።
የኢህአዴግ አገዛዝ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ የሀገራቱ ግንኙነት እንደገና ዳግም መጀመሩንም ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መልካም የነበረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ባለፉት ሦስት ዓመታትም እየተዳከመ መምጣቱን አንስተዋል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ቆርጦ በመነሳቱና የአሜሪካን ጥያቄዎች ከሀገር ጥቅም አንጻር መዝኖ ማየት በመጀመሩ ነው ይላሉ፡፡
ከዚህም ባለፈ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት አሜሪካኖች ጣልቃ ለመግባት ሲሞክሩ ኢትዮጵያ ጉዳዩ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ፅኑ አቋም ይዛ በመቀጠሏ ግንኙነታቸው ሻክሮ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ቆይታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ተቀዛቅዞ የቆየውን የሀገራቱን ግንኙነት በማደስ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ይህም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የተዳከመ ግንኙነት ለማደስ ቆርጣ መነሳቷን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
ይህም በሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን በማንሳት።
አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ አገራቱ የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ትብብርን የሚያሳድጉ መግባባቶች ላይ መድረሳቸውን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ለዚህም በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤድ) በኩል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 331 ሚሊዮን ዶላርና ተጨማሪ ምግብ ነክ ድጋፍ እንደምትደርግ ቃል መግባቷን ጠቅሰዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ በተለይ ለግብርና ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ አሁንም አጠናክራ መቀጠሏን የተናገሩት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ፤ ይህም የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከሩን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ በተለይም አልሸባብን በመዋጋት ያላትን ሚና አሜሪካ ትልቅ ስፍራ እንደምትሰጠውና በቀጣይም ሽብርተኝነትን በመዋጋት አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በራሳቸው አቅም ቀጣናዊ የፀጥታና ደህንነት ሥራን ለማከናወን እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ አሜሪካ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ አዲስ ትብብር ለመፍጠር አስባ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድርጓንም ነው ያነሱት።
ለዚህም አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚደረገውን የሀገራቱን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ መጥቀሳቸው የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።