ውጣ ውረድ የማይበግረው አጋርነት

1424

በሰለሞን ተሰራ

ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ቀደምትና ታሪካዊት ሀገር ነች። ቅሉ ከውጭ ሀገራት ያላትን   ዘመናዊው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቅኝት የጀመረችው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ መሆኑ በታሪክ ይጠቀሳል።

በተለይም ኢጣሊያ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1896 በአድዋ እንዲሁም በድጋሚ በ1935 ያደረገችው የግፍ ወረራ ኢትዮጵያ የዓለምን ፖለቲካ በቅጡ አሰላለፍ ተረድታ አጋር ሀገራትን እንድትሻ ዐይኗን ገልጦላታል።

በዚህም ድኅረ-አድዋ ድል በርካታ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መስርተዋል።

የወቅቱ ልዕለ-ኃያል ሀገር አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ የተመሰረተውም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና በፕሬዝዳንት ሩዝቬልት መንግሥት ተወካይ ሮበርት ስኪነር መካከል በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1903 በተደረሰው የንግድ አጋርነት ስምምነት ነበር። 

ድኅረ-ስምምነቱም በፈረንጆቹ በ1909 የአሜሪካ ሌጋሲዮን በአዲስ አበባ የተመሰረተ ሲሆን ሆፍማን ፊሊፕ የተባሉት ቋሚ መልዕክተኛ የአሜሪካ ቆንስላ ተሿሚ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአፄ ምኒልክ አቅርበዋል፡፡

ከ120 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጽኑ ወዳጅነትና የጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ እንደነበር ይወሳል፡፡ 

ሀገራቱ ጥቅማቸውን በጠበቀ መልኩ የመሰረቱት ግንኙነት ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራን ተከትሎ ቆንስላዋን የዘጋችው አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ በአርበኞቿ ትግል ነፃነቷን ስታረጋግጥ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በነኅሴ 1943 በድጋሚ ቆንስላዋን በመክፈት ግንኙነቷን አስቀጥላለች።

በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የቆንስላ ቢሮ ከፍታ ዕውቁን ዲፕሎማት ብላታ ኤፍሬም ተወልደመድኅንን በቋሚ መልዕክተኛነት ሾማለች።

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1952 የተደረገው 'ፖይንት ፎር' የተሰኘው የተቋማት ቴክኒክ ድጋፍ ስምምነት ለሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ መሰረት የጣለ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ስምምነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅት በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ተቋቁመዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነቱ አድማሱን እያሰፋ፣ ሥር እየሰደደ ቀጥሎ ኢትዮጵያ ጦር ሠራዊቷን እንድታጠናክር በአነስተኛ የጦር መሳሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎችና ወታደራዊ ሥልጠናዎች ተጨባጭ አጋርነት አሳይታለች።

የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን በተቆጣጠረ ማግስት ግን በዘመኑ በነበረው ዓለም አቀፋዊ ርዕዮተ- ዓለም ልዩነት ሳቢያ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሮ ሌላ መልክ ያዘ።

በተለይም የደርግ ሊቀ-መንበር የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ወደ ሶቪየት ሕብረት አቅንተው የጦር መሳሪያ ድጋፍ መፈራረማቸው አለመግባባቱን ይበልጥ አባባሰው።

በዚህም አሜሪካ በኤርትራ የነበረውን የቃኘው ሻለቃ ጣቢያዋን ዘግታ ወጣች። ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ከአምባሳደር ደረጃ በማውረድ በጉዳይ አስፈጻሚ ሲገናኙ ቆይተዋል፡፡

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የሀገራቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት የአምባሳደር ደረጃ በመመለስ ከአሜሪካ ጋር የነበረው ግንኙነት መልሶ እንዲያንሰራራ አድርጎታል፡፡

ባለፉት 30 ዓመታት አሜሪካ በጤና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ በምታደረገው ድጋፍ በመታገዝ በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት ወዲህ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አሜሪካ መርህን ያልተከተለ አካሄድ በሀገራቱ መካከል የነበረውን ወዳጅነትና አጋርነት ላይ ጥቁር ጥላ ማጥላቱ አይዘነጋም፡፡

ነገር ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት በማደስ የነበረውን ጠንካራ ወዳጅነት በድጋሚ  የሚያጸኑ ጅማሮዎች ተስተውለዋል።

በተለይም ጥቅምት 23  ቀን 2015 ዓ.ም. በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተደረሰውን የሰላም ሰምምነት ተከትሎ የሀገራቱ መቃቃር እየረገበ ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ እየጎበኙ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተነጋግረዋል። 

አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ያደረጉት ውይይት ዘርፈ-ብዙ አጋርነትን ለማጠናከር መግባባት የተደረሰበት እንደነበርም በሁለቱም ወገኖች ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውይይቱ በተለያዩ የሀገር ውስጥ፣ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነና በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ስምምነት የተደረሰበት እንደሆነ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ ላይ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት ተቀባይነት ማግኘቱንም ጠቅሰዋል። 

በኢኮኖሚው መስክ በተለይም በግብርና እና በቀጣናዊ መረጋጋት ላይ ባተኮሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት መነጋገራቸውን በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ አንቶኒ ብሊንከን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መክረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሚኒስትሮቹ ለረዥም ዘመን የዘለቀውን የኢትዮ-አሜሪካ ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ተነጋግረዋል።

በኢትዮጵያ አዲስ የመረጋጋትና የሰላም ምዕራፍ መከፈቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አብራርተውላቸዋል።

የሰላም ምዕራፍ የበለጠ እንዲጠናከርና የሰመረ እንዲሆን ከዚህ ባለፈም የሀገሪቱን በጎ ገጽታ እንዲላበስ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እምርታ እንዲመጣ ለሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚነት መንግሥት አሁንም ቁርጠኛና ጠንካራ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፤ በመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋም ተግባር የአሜሪካ መንግሥት እንዲደግፍም ጠይቀዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው፤ የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር አሜሪካ በትብብር መንፈስ እንደምትሰራ እና አሜሪካ ሁለንተናዊ ድጋፏን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።

አሜሪካ ለድርቅ ተጎጂዎች እና ለስደተኞች የምታደርገው ድጋፍ አለመቋረጡ የሁለቱ ሀገራት አብሮነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ይጠቁማል፡፡

የብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት ከኢትዮጵያ መጀመሩም ዛሬም ኢትዮጵያ በአሜሪካ መንግሥት ዐይን ያላትን ቀዳሚ ሥፍራ ያመለክታል።

አንቶኒ ብሊንከን የሰላም ትግበራ ሂደቱ በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ የበለጠ እንዲጠናከር የአሜሪካ መንግሥት ሁለገብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እያደረገች ያለውን ጥረት አሜሪካ በአድናቆት እንደምትመለከተውና የሚበረታታ መሆኑን ብሊንከን ገልጸዋል።

የብሊንከንን ጉብኝት ተከትሎ አሜሪካ 331 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንደምታደርግ አረጋግጣለች። ድጋፉም በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች ነፍስ አድን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም