ቀጥታ፡

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የሰጡት ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ተቀባይነት የለውም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ)፦“የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክተው የሰጡት ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግደብ የሶስትዮሽ ድርድር ሁሉንም አሸናፊ ባደረገ መልኩ እንዲቋጭ አሁንም ቁርጠኛ መሆኗን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” በሚል ግድቡን አስመልክቶ የሰጡትን “ኃላፊነት የጎደለው” መግለጫ ኢትዮጵያ እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

“ይህን አይነት ማስፈራሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር እና የአፍሪካ ሕብረት የመተዳደሪያ ደንብን በከፍተኛ ሁኔታ የጣሰ ነው” ብሏል።

መግለጫው እ.አ.አ መጋቢት 23/2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተፈራረሙትን የመርሆዎች ስምምነት በግልጽ መጣሱንም ገልጿል።

ግብጽ “ድፍረት የተሞላባቸው እና ሕጋዊ ያልሆኑ” መግለጫዎችን ከመስጠት መቆጠብ እንደሚገባት ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

ሁሉም የሚመለከተው አካል ግብጽ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የሚመሩባቸውን መርሆዎች በግልጽ እየጣሰች መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባና “በዛቻ እና ማስፈራሪያ” የትኛውንም አይነት ፍላጎት ማስፈጸም እንደማይቻልም አስገንዝቧል።

“በመልካም ሀሳብ እና ዓለም አቀፍ ሕግን በማክበር በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የሚመራውን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ማካሄድ ከተቻለ ሁሉንም በሚያስማማ መልኩ መፍትሔ ማግኘት ይቻላል” ነው ያለው ሚኒስቴሩ።

በድርድሩ የሚሳተፉ አካላት ወደ አፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ዳግም በመመለስ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውይይት ላይ መሰረት ያደረገ መፍትሔ ላይ እንዲደረስ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ የግድቡ ድርድር ሁሉንም አሸናፊ ባደረገ መልኩ እንዲቋጭ አሁንም ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም