ስልጠናው አቅማችንን በማጎልበት አገራዊ ነባራዊ ሁኔታውን ተረድትን ለቀጣይ ሥራ እንድንተጋ የሚያነሳሳን ነው--የወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ስልጠናው አቅማችንን በማጎልበት አገራዊ ነባራዊ ሁኔታውን ተረድትን ለቀጣይ ሥራ እንድንተጋ የሚያነሳሳን ነው--የወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት
ባህር ዳር መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ) በከፍተኛ አመራሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና አቅማችንን በማጎልበት አገራዊ ነባራዊ ሁኔታውን ተረድትን ለቀጣይ ሥራ እንድንተጋ የሚያነሳሳን ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።
ስልጠናው ወጣቶቹ ለነገ አመራር የሚሆኑበትን አቅም ለመገንባት እንደሚያስችል የሊጉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ፈዲላ ቢያ አስታውቃለች።
ከኦሮሚያ ክልል የመጣው የስልጠናው ተሳታፊ ወጣት ገዛኸኝ አንዳርጌ ለኢዜአ እንደገለጸው ''ወጣቶች የአገራችን ሉአላዊነት በማስጠበቅና የህዝባችን አንድነት በማጠናከር ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ ኃላፊነት አለብን።
እስካሁን በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እሳቤዎች፣ በአዲስ እይታ እና አስተሳሰብ የዘመናዊው ዓለም የኮሙዩኒኬሽን ስልት በሚሉ ርዕሶችና በዓለም ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግሯል።
የነገ አገር ተረካቢ ወጣቱ በመሆኑ በስልጠናው አቅምንና ክህሎትን ከማሳደግ ባሻገር ቁርጠኝነትን ተላብሶ ራስን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
በአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መብታቸው ተከብሮ ከልዩነት ይልቅ በአብሮነት መኖር በሚችሉበት ላይ በስልጠናው ተገቢውን እውቀትና ክህሎት እየጨበጠ መሆኑን ገልጿል።
"የሊጉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አብዛኛው አዳዲስ በመሆናችን እንደዚህ ዓይነት የአቅም ግንባታ ስልጠና አስፈላጊና ወቅታዊ ነው" ያለችው ደግሞ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመጣችው ወጣት ዝናሽ ኃይለማርያም ናት።
ስልጠናው ኢትዮጵያ እየገጠሟት ያሉ ችግሮችን ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ለመፍታት ወጣቱ ሚና የሚጫወትበት አቅም የሚገነባበት ነው ብላለች።
የፓርቲውን የፖለቲካ መርሆዎች በማወቅ፣ በአዲስ የፖለቲካ እይታ ራስን በመቃኘት እና ተግባቦትን በማሳደግ እስከታችኛው መዋቅር ወጣቶችን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት የስልጠናው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግራለች።
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ፈዲላ ቢያ በበኩሏ ስልጠናው በገለጻ፣ በቡድን ውይይትና በዋና ዋና ሃሳቦች ላይ በከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ማብራሪያ ተደግፎ እየተሰጠ መሆኑን ተናግራለች።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበላይ አመራር ከሚሰጣቸው ማብራሪያ በተጨማሪ በነጻነት እየጠየቁ፣ ሃሳብ እያንሸራሸሩና የሚያውቁትን በመመለስ ስለሚሳተፉ የሃሳብና የአመለካከት አንድነት እየያዙ መሆናቸውን ገልጻለች።
"ሰልጣኞቹ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጣን መሆናችን ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን በማጎልበት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ብላለች።
በዚህም ወጣቱ ከመከፋፈል አንድነትን፣ ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከመገፋፋት መተሳሰብን በመምረጥ በጋራ ለኢትዮጵያ መቆምና ሀገርን መገንባት እንዳለበት ግንዛቤ የተገኘበት መሆኑን ገልጻለች።
በባህር ዳር ከተማ "በወጣቶች አቅም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ይረጋገጣል!” በሚል መሪ ሃሳብ እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ከሁሉም ክልሎች የመጡ 223 የሊጉ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።