ኤሌክትሮኒክ የመንግስት ስትራቴጂና ኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር ጥናት እና ትግበራ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

632

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ)፦ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንግስት አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ኤሌክትሮኒክ የመንግስት ስትራቴጂና ኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር ጥናት እና ትግበራ ፕሮጀክት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆነ።

ኤሌክትሮኒክ የመንግስት አገልግሎት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንግስት የአገልግሎቶችን በቀጥታ ባሉበት ለዜጎች፤ ለንግድ ተቋማትና ሌሎችም ተገልጋዮች ተደራሽ ማድረግን ያለመ ነው።

በመንግስት እና በሌሎች በሚመለከታቸው አካላት መካከል ፈጣንና አስተማማኝ የዳታ እና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ማስቻልን እንዲሁም ተቋማት የውስጥ ስራቸውን በቴክኖሎጂ አስደግፈው በሚገባ እንዲያከናወኑ ማድረግንም ያካትታል።


 

በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ፤ ፕሮጀክቱ የመንግስትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

የዲጂታል ተጠቃሚነትን በማስፋት በ2025 ሁሉም የመንግስት ተቋማት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ስርዓት በማሳለጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲያሳድጉ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኤሌክትሮኒክ የመንግስት ስትራቴጂ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት በማቅረብ የዲጂታል አጠቃቀምን ማሳደግ ሲሆን ብልሹ አሰራርን ለማስወገድና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማስተካከል ይጠቅማል ብለዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ ይህ አይነቱ ስትራቴጂ "ዲጂታል ኢትዮጵያን" ለማሳካት ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግ የግሉን ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችልም ነው የገለጹት።

የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የተቋማት አገልገሎት ፈጣንና የተቀላጠፈ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።


 

መንግስት እየተገበረው ባለው የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የአይ.ሲ.ቲ. እና የዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የዕቅዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የልማት ስራዎች በጥናት ለይቶ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።


 

የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ እና መሰረተ ልማት ቡድን መሪዋ ሳኔ ዊሊያም፤ ህብረቱ ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸውን የልማት ስራዎች በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ስትራቴጂው ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግስት አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ አድንቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለመንግስት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ተደራሽነት እና ሌሎች የቢዝነስ ስራዎች የሚውል የ10 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንግስት አገልግሎቶችን በቀጥታ ባሉበት ለዜጎች፤ ለንግድ ተቋማት እና ለሌሎች ተገልጋዮች ተደራሽ ማድረግን ያለሙ ሁለት ፕሮጀክቶችን እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2015 እና ከ2016 እስከ 2020 ተግባራዊ አድርጋለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም