በጤፍ ምርት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በምርት እጥረት ሳይሆን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች የፈጠሩት ችግር መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጤፍ ምርት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በምርት እጥረት ሳይሆን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች የፈጠሩት ችግር መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ)፦ ሰሞኑን በጤፍ ምርት ላይ የታየው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በምርት እጥረት ሳይሆን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች የፈጠሩት ችግር መሆኑ ተገለጸ።
የጤፍና ሌሎችም የግብርና ምርቶችን በመደበቅ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በሚሰሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፣ የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ እና የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን በዚሁ ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሰሞኑን በጤፍ ምርት ላይ የታየው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በምርት እጥረት ሳይሆን ሕገ- ወጥ ነጋዴዎች ምርት በመደበቃቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሀመድ፤ በጤፍ ምርት ላይ የተከሰተው የዋጋ ንረት በምርት እጥረት ሳይሆን በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የፈጠሩት ችግር መሆኑን ገልጸዋል።
በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችና ደላሎች በፈጠሩት የገበያ አሻጥር የተከሰተውን የምርት እጥረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን እልባት እንዲያገኝ እየሰራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የሕብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር፣ ያልተገባ የምርት ክምችት የፈጠሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ገበያውን ለማረጋጋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርት አቅርቦትና የግብይት ሥርዓቱን የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን የመፍታት ሥራም በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ገሾ፤ የምርት አቅርቦትና ግብይቱን የሚያበላሹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎችን በማጋለጥ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች በስተቀር ማንኛውም ነጋዴ ምርቶችን በየትኛውም አካባቢ ማንቀሳቀስ እንደሚችልም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ዑመር፤ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ምርት በመደበቅና ወደ ውጭ በማስወጣት የንግድ ሥርዓቱን ለማዛባት እየሰሩ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር በገበያው ላይ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ፤ የጤፍና የስንዴ ምርት የሚደብቁና ያልተገባ ጭማሪ የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።