በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚካሄደው የወርቅ ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

መንጌ መጋቢት 07 /2015 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚካሄደው የወርቅ ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጥ የክልሉ አካባቢ ደን ሃብት ጥበቃና የአየር ንብረት ባለስልጣን አመለከተ።

በክልሉ አሶሳ ዞን  መንጌ ወረዳ የባህላዊ ወርቅ አመራረት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

ከመስክ ምልከታ በኋላ በመንጌ ከተማ ውይይት ሲጀመር የክልሉ አካባቢ ደን ሃብት ጥበቃና የአየር ንብረት ባለስልጣን ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም ሙሳ  እንዳሉት፤ ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ሃብት መካከል ወርቅ ዋነኛው ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ወርቅ አመራረት የአካባቢ ተጽዕኖ አዋጅ ሊከተል እንደሚገባ አስገንዝበው፤ በተለይም በባህላዊ ወርቅ ማምረት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ማህበራት እና ድርጅቶች ተሠማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ማህበራትና ድርጅቶች የአካባቢ ተጽዕኖ አዋጅን ተግባራዊ እያደረጉ እንዳልሆነ አመልክተው፤ ይህም ወርቅ የሚመረትባቸው አብዛኞቹ ወረዳዎች የአፈር መሸርሸርን ጨምሮ የአካባቢ ጉዳት እንዳስከተለ ጠቁመዋል።

የአካባቢ ተጽዕኖ አዋጅ አተገባበር ችግር በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ጭምር እንደሚታይ ጠቁመው፤ በወርቅ ልማት ሆነ በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሠማሩ ህጉን አክብረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት በማልማት የአካባቢ ጥበቃ ህግን ተግባራዊ ማድረግ የግድ መሆኑን አቶ አብዱልከሪም አሳስበው፤ ቢሮው ግንዛቤ ማስጨበጥን በማስቀደም እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል::

የመንጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም መንሱር በበኩላቸው በወረዳው ወርቅ በሚመረትባቸው አካባቢዎች የተፈጥሮ ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው ሲሉ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ለመፍትሄው እንደሚሠራ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በቢሮው የአካባቢ ህግ ተከባሪነት እና ተጽዕኖ ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታፈረ የአካባቢ ተጽዕኖ አዋጅ መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል።

ወርቅ አምራቾች አፈሩን ወደቦታው ከመመለስ ጀምሮ እንክብካቤ ማድረግ እንዳለባቸው እንደሚያስገድድ ባቀረቡት ጽሁፍ ገልጸዋል።

በውይይቱ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ወርቅ አምራቾች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም