ኢትዮጵያና ሱዳን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ /አይ.ሲ.ቲ/ እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

602

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሱዳን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ /አይ.ሲ.ቲ/ እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ እና የሱዳን የቴሌኮሙኒኬሽንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሚኒስትሩ አድል ሐሰን መሐመድ ፈርመውታል።

አገራቱ ያካበቱትን የቆየ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ዛሬ በጋራ ለመስራት የተፈጸመው ስምምነትም አገራቱ በአይ.ሲ.ቲ. እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች በትብብር እንዲሰሩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ የሁለቱም አገራት ዜጎች የዲጂታላይዜሽን አጠቃቀም እንዲያድግ በትኩረት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

የሱዳን የቴሌኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሚኒስትሩ አድል ሐሰን፤ ሱዳን በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የአይ.ሲ.ቲ እና ዲጂታላይዜሽን ልማት ትምህርት በመውሰድ ተግባራዊ ማድረግ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።


 

በኢትዮ-ሱዳን መካከል የተደረገው የሥራ ስምምነት የአገራቱን ትብብር በማሳደግ የጋራ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።

የሥራ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የጋራ ቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች በትብብር የሚሰሩ አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአገራቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ምኅዳር በማስፋት የዜጎችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የዛሬው ስምምነት ጠቃሚ ነው ብለዋል።


 

ስምምነቱ ኢትዮ-ሱዳን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በአይ.ሲ.ቲ. ዘርፍ በትብብር እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሪባ ናቸው።

ስምምነቱ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን የቴሌኮሙኒኬሽን እና የመገናኛ ብዙኃን ድንበር ዘለል ችግሮች ለማስተካከል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆንም በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱን አገራት ዜጎች የቴሌኮም አገልግሎት ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም