ቀጥታ፡

በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚላከው ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ እየተደረገ ነው- የቦረና ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ግብረ ኃይል

መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ)፦በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ  ዜጎች  የሚላከው ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ  የማድረግ ስራ መቀጠሉን የቦረና ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

ግብረ ኃይሉ በአራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና በኦሮሚያ ክልል ተጠሪ ቢሮዎች የተዋቀረ ሲሆን፤ በዋናነት ወደ ዞኑ የሚላኩ ሰብዓዊ ድጋፎች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆናቸውን ይቆጣጠራል፡፡


 

ግብረ ኃይሉ በቦረና ዞን 13 ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር የሰብዓዊ ድጋፉን ተደራሽነት አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

በዚህም ወደ ዞኑ የሚላኩ የሰብዓዊ ድጋፎች፣ ቁሳቁሶችና አልሚ ምግቦች ለህብረተሰቡ በአግባቡ ተደራሽ ስለመሆናቸው ግብረ ኃይሉ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡


 

በዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ ደምስ ሹሜ፤ ግብረ ኃይሉ ዝርዝር ቼክ ሊስት በማዘጋጀትና በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ የመስክ ምልከታ ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ሰብዓዊ  ድጋፉ ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ድጋፉ በችግር ወስጥ ለሚገኙ ወገኖች እየተከፋፈለ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፤ በመስክ ምልከታው በተለያዩ አካባቢዎች የአቅርቦት እጥረት በመታየቱ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲጓጓዝ እየተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በቦረና ዞን ዱቡሉቅ ወረዳ ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች በመንግሥት እና ከአጋር አካላት የሚደረገው ድጋፍ እየደረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

የቦረና ዞን ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ሊበን ሶራ፤ ወደ ዞኑ የሚመጣው ደጋፍ ለህብረተሰቡ በትክክል መድረሱን የሚከታተልና የአገር ሽማግሌዎች የሚመሩት ኮሚቴ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም