ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሁለት ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ ማዳበሪያ፣ ጸረ አረምና ጸረ ተባይ ኬሚካል በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን  ሁለት ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ ማደበሪያ፣ ጸረ አረምና ጸረ ተባይ ኬሚካል በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ገለጸ ፡፡

በኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለ2015/2016 የምርት ዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብዓቶችንና የሜካናይዜሽን እርሻ መሳሪያዎችን እያቀረበ ይገኛል።

አርሶ አደሮች ለፈሳሽ ማዳበሪያ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት አንድ ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ ማዳበሪያ ከውጭ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ እያሰራጨን ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ሊትር ጸረ አረምና ጸረ ተባይ ኬሚካል ለአርሶ አደሩ በመቅረብ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ተጨማሪ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ፈሳሽ ማዳበሪያና ጸረ ተባይ ኬሚካል ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል።


 

የፈሳሽ ማዳበሪያውን ጨምሮ እየቀረቡ ያሉ ግብዓቶችም የሰብል ጤና አጠባበቅ እና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ነው ያብራሩት።

አቶ ፈለቀ አክለውም ኮርፖሬሽኑ ትራክተርና መሰል የሜካናይዝድ እርሻ መሣሪያዎችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከውጭ በማስመጣት ለተጠቃሚዎች በኪራይና በሽያጭ እያቀረበ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት 46 ትራክተሮችን ለተጠቃሚዎች ያቀረበ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም 111 ትራክተሮችን ከውጭ በማሰገባት ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፤ ከ1 ሺህ በላይ በትራክተር የሚጎተቱና ባለ ሞተር የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን ጨምሮ ማረሻዎች፣ መከስከሻ፣ ማዳበሪያ መበተኛ፣ ዘር መዝሪያ እና መስመር ማውጫዎችም ከውጭ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሀገሪቱ መልክአ ምድር እና አየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ጥራት ያላቸውን የእርሻ መሣሪያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ፈለቀ ገልጸዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም