በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
ባህር ዳር መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኃይለሚካኤል ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ከ2004ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በእዚህም እስካሁን ድረስ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማዋጣት ህዝቡ የራሱን አሻራ ማስቀመጡን አመልክተዋል።
"ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለግድቡ ግንባታ ገቢ የማሰባሰብ ሥራው ተቀዛቅዞ ቆይቷል" ብለዋል።
የተቀዛቀዘውን ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እንደገና በማነቃቃት ዘንድሮ 20ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አቶ ኃይለሚካኤል ጠቅሰዋል።
በእዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀሙን ነው ኃላፊው ያመለከቱት።
ባለፉት ዓመታት ግድቡ በደለል እንዳይሞላ መላው የክልሉ ህዝብ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በችግኝ ተከላ ሥራዎች በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም አቶ ኃይለሚካኤል ተናግረዋል።
እንደሀገር በተጀመረው 2ኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ ጉዞም ደብረ ማርቆስ እና ጎንደርን ጨምሮ በስምንት የክልሉ ከተሞች ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርግ ቅስቀሳ መደረጉን ገልጸዋል።
ለግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከመጋቢት 15 እስከ 30 ቀን 2015ዓ.ም ተጨማሪ ገንዘብ በቦንድ ግዥ ለማሰብሰብ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማፋጠን እየተደረገ ላለው ጥረት መላው የክልሉ ህዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊ ጥሪ አቅርበዋል።
"የግድቡ መጠናቀቅ ኢንዱስትሪዎች በቂ ኃይል አግኝተው ምርታቸውን እንዲያሳድጉ፣ ህዝቡ ከጨለማ እንዲወጣ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ያሉትና በቦንድ ግዥ እየተሳተፉ የሚገኙት የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ አበባው መንግስቱ ናቸው።
የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ አገራት በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
"ለሕዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛት የጀመርኩትን ድጋፍ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ አጠናክሬ ለመቀጠል ዝግጁ ነኝ" ሲሉም አቶ አበባው አክለዋል።
አቶ የእኔገዳም ተስፋ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዘመናችን መላ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ ጫፍ ያነቃነቀና ያስተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል።
"የሕዳሴው ግድብ እንደ አድዋ ድል አንድነታችንን ያጠናከርንበትና አዲስ ታሪክ ለዓለም የምናበስርበት ነው" ብለዋል።
"እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለያየ ጊዜ በወር ደመወዜ ቦንድ በመግዛት ለግድቡ አሻራዬን አስቀምጫለው" ያሉት አቶ የእኔገዳም፣ በቀጣይም ለግድቡ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።