የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሳምንቱ የነበሩ ዋና ዋና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ የነበራቸው ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ አየተሸጋገረ መሆኑን አመላካች መሆኑንም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተለያዩ የአገር ውስጥ፣ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስለመመካከራቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በመግባባትና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ቃል-አቀባዩ በሰላም ዲፕሎማሲ ላይ በማትኮር ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።
በተለይ ማስገንዘብ እና ወዳጅ ማብዛት ላይ በተሰራው ጠንካራ ስራ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው ውጤታማ ስራዎች እየተመዘገቡበት መምጣቱን ተናግረዋል።