በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅን ለማሳደግና የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅን ለማሳደግና የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ መጋቢት 7/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅን ለማሳደግና የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
ለሰው ልጆች ጤና መጠበቅ ወሳኝ ለሆነው የአካባቢ፣ የእንስሳት፣ የውሃና የከባቢ አየር ጤናማነት ትኩረት መስጠት ላይ ያተኮረ "የአንድ ጤና" ስትራቴጂ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሒዷል።
በምክክር መድረኩ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በምክክሩ ላይ ጥናት ያቀረቡት በታንዛኒያ የአሩሻ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ቲኦ ናይት-ጆንስ፤ የማህበረሰብ ጤና ከእንስሳት፣ ከከባቢ አየር፣ ከውሃ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው ብለዋል፡፡
ለአብነትም 70 በመቶ የሚሆኑት በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው፤ ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የበሽታዎች ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው ጥናት አቅራቢው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅትም በተለይ የከባቢ አየር መለዋወጥ ችግሩን ይበልጥ እያባባሰው ነው ይላሉ ዶክተር ቲኦ ናይት።
የእንስሳት፣ የእጽዋት እና የአካባቢ ጤና ካልተጠበቀ ማሕበረሰቡ በበሽታ የመጠቃት እድሉ የሰፋ እንደሆነም አመልክተዋል።
በመሆኑም ተላላፊ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም፣ ስርጭታቸውን ለመቀነስ፣ ለአካባቢ፣ ለእንስሳት ለውሃና ለአየር ጤንነት መጠበቅ ተቋማት በትብብር መስራት እንደሚጠባቅባቸው አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ አንድ ጤና አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ፈይሳ ረጋሳ ፤ የአንድ ጤና መርሃ-ግብር ሀገራዊ የጤና ስጋቶችን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ የአንድ ጤና መርሃ ግብርን ቀርጻ እየተገበረች መሆኑን ጠቁመው በተለይ "አባ ሰንጋ እና የእብድ ውሻ" በሽታን ከመከላከል አንፃር ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ነው ያብራሩት።
በቀጣይም ብሔራዊ ኮሚቴው ለህብረተሰቡ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የአንድ ጤና ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በቅንጅት እና በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ11 የአፍሪካ ሀገራት እየተተገበረ ሲሆን በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ተመራማሪው ዶክተር ሚርጊሳ ካባ የማህበረሰብ ጤና ችግርን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት።
ዩኒቨርሲቲው ለአንድ ጤና አሰራር ተፈጻሚነት በተለይ በጥናትና ምርምር ስራው የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡