ቀጥታ፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ጉብኝት አጠናቀው ተመለሱ

አዲስ አበባ መጋቢት 07/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቆይታቸውን አጠናቀው ዛሬ ተመልሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ  በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።


 

አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተለያዩ የአገር ውስጥ፣ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ተስማምተዋል።

በውይይቱ በኢኮኖሚ፣ በልማት ጥረቶች፣ በተለይም በግብርናና ቀጣናዊ መረጋጋት ላይ ያሉ ጉዳዮችም ትኩረት እንደተሰጠባቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።


 

በተጨማሪም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በተለያዩ  ጉዳዮች ላይ  መክረዋል።

አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 331 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ጠቁመዋል።

አሜሪካ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እንዲጠናከር እያደረገች ያለውን ድጋፍ በተለያዩ መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1903 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም