"የሠላም ሥምምነቱ የአፍሪካ የመሪነት ሚና ጥቅም የታየበት ነው"-አንቶኒ ብሊንከን - ኢዜአ አማርኛ
"የሠላም ሥምምነቱ የአፍሪካ የመሪነት ሚና ጥቅም የታየበት ነው"-አንቶኒ ብሊንከን
አዲስ አበባ መጋቢት 6/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው የሠላም ሥምምነት የአፍሪካ የመሪነት ሚና ጥቅም የታየበት ነው ሲሉ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ገለጹ።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት የአፍሪካ የመሪነት ጥቅም የታየበት ነው ብለዋል።
ሥምምነቱ የሰዎችን ህይወት በመታደግና ህይወታቸውን በአዎንታዊ መልክ በመቀየር የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ በማድረግ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል።
ሥምምነቱ የነበረውን ግጭት እንዲቆምና ሰብዓዊ ድጋፉን በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ይበልጥ እንዲሳለጥ አስችሏል ነው ያሉት።
ያም ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ የተቋረጡ የሕዝብ አገልግሎቶች ዳግም እንዲመለሱና የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የፌዴራል መንግሥቱና ሥምምነቱን የፈረሙት የሕወሃት መሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
በተጓዳኝም፤ የአፍሪካ ኅብረት፣ የኬንያና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት ላበረከቱን አስተዋጽዖም እውቅና ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር በሰላም አተገባበሩ ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመታት በምግብ ዋስትና እንዲሁም በሰብዓዊ እርዳታ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓንም ተናግረዋል።
አሁንም ደግሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 331 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓን ጠቁመው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አሜሪካ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እንዲጠናከር እያደረገች ያለው ድጋፍ በተለያዩ መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።