ቀጥታ፡

የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት በሥነ-ልቦና፣ በታሪክና ባህል ባለሙያዎች እንዲሁም በኃይማኖት አባቶች እንዴት ይታያል?

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2015 (ኢዜአ) የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት በሥነ-ልቦና፣ በታሪክና ባህል ባለሙያዎች እንዲሁም በኃይማኖት አባቶች እንዴት ይታያል?

በብሔራዊ ሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ባሳለፍነው ሳምንት የግብዓት ማሰባሰብ መድረክ መጀመሩ ይታወሳል።

በዛሬው ዕለትም የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የሥነ-ልቦና፣ የታሪክና ባህል ባለሙያዎች እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከታሪክ፣ ከሥነ-ልቦናና ከሃይማኖት አኳያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ የፍትሕ ጉዳይ በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል። 

እርቅና ምህረትን ማምጣት የሚቻለው ፍትህ ስፍራውን ሲይዝ መሆኑን በመግለጽ።


 

የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሠብለ ኃይሉ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ጥፋቶች እልባት ባለመሰጠቱ ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንንም በሽግግር ፍትሕ ሂደት በማከም መሻገር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለዚህም ፍትሕ ሳይዛባ፤ በገለልተኛ፣ ለአገርና ለህዝብ በሚቆረቆሩና አዋቂ ባለሙያዎች የተመራ የሽግግር ፍትህ ለማካሄድ መወሰኑ ከግለሰብ እስክ አገር ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።


 

የቀድሞ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ልዑል በዕደማርያም መኮንንና የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባል ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ የሽግግር ፍትሕ ማስፈጸሚያ ፖሊሲ ለማዘጋጀት መታሰቡ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

በውይይት የማይፈታ ችግር እንደሌለ በመግለጽም፤ ፖሊሲው በማህበረ-ኢኮኖሚው ዘርፍም ሁነኛ አገራዊ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን ጠቁመዋል።

የትላንትን ችግር ፈትሾ በሽግግር ፍትህ መፍትሄ በመስጠት የተሻለ ነገን መገንባት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብለዋል።


 

አስተያየት ሰጪዎቹ የሽግግር ፍትሕ ሁሉንም ያሳተፈ በማድረግ ለህዝብ እፎይታ በሚሰጥ አግባብ መከወን እንዳለበት ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትህ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም