በክልል ምክር ቤቶች መካከል የተደረገው የልምድ ልውውጥ ለስራችን አቅም ይፈጥራል--የክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች - ኢዜአ አማርኛ
በክልል ምክር ቤቶች መካከል የተደረገው የልምድ ልውውጥ ለስራችን አቅም ይፈጥራል--የክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች
ጋምቤላ መጋቢት 6/2015 (ኢዜአ) በክልል ምክር ቤቶች መካከል የተደረገው የልምድ ልውውጥ ለክትትልና ቁጥጥር ስራቸው አቅም እንደሚፈጥርላቸው የየክልሎቹ አፈ-ጉባኤዎች ገለጹ።
የክልል ምክር ቤቶች የአፈ-ጉባኤዎች የጋራ ፎረም በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የልማትና የቱሪስት መስብ ቦታዎችን በመጎብኘት የተሞክሮና ልምድ ለውውጦችን እያደረጉ ነው።
አፈ-ጉባኤዎቹ እንዳሉት የሚያካሂዱት የተሞክሮ ልውውጥ የክትትልና ቁጥጥር ስራቸውን በማጠናከር ከህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አቅም እየፈጠረላቸው ነው።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዓለምነሽ ይባስ በሰጡት አስተያየት የአፈ-ጉባኤዎች ፎረም አንዱ ክልል ከሌላው ክልል መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን እያጠናከረ ነው ብለዋል።
ፎረሙ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለመገምገም ልምድ የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሲያ ከማል በበኩላቸው የጋራ ፎረሙ አንዱ ከአንዱ ልምድ በመውሰድ በክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች በመፍታት ረገድ ትልቅ ውጤት ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
የአፈ-ጉባኤዎች የጋራ ፎረም የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ረገድም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የአፈ-ጉባኤዎች የጋራ ፎረም በህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተደረጉ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን ተሞክሮ የሚወስዱበት መድረክ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ ገልጸዋል።
የልምድና ተሞክሮ ለውውጡ የአሰራር ለውጦችን እያመጣ በመሆኑ የክልል ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች የጋራ ፎረም በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አፈ-ጉባኤዎቹ በክልሉ የአቦቦ ወረዳን ባህላዊ ወርቅ ማምረቻ፣ የአሌሮ ግድብን፣ የባሮ ድልድይንና ሌሎች የልማትና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።