ቀጥታ፡

በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ 40  የውሃ መሳቢያ  ፓምፖች ለጉራጌና ስልጤ ዞን አርሶ አደሮች  ድጋፍ ተደረገ

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 06 / 2015 (ኢዜአ)፡- በተሳትፋዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም 14 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው  በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ 40  የውሃ መሳቢያ  ፓምፖች  በደቡብ ክልል  ለጉራጌና ስልጤ ዞን አርሶ አደሮች  ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ርክክብ በተደረገበት ወቅት በክልሉ ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ምራ መሐመድ እንዳሉት፤ ፓምፖቹ መደበኛ የመስኖ ተቋማት ግንባታ ባልተዳረሰባቸው በጉራጌ ዞን ማረቆ ወረዳ እንዲሁም  በስልጤ ዞን  ላንፍሮና ሳንኩራ ወረዳዎች አርሶ አደሮች የሚውሉ ናቸው።

ወረዳዎቹ   ዝናብ አጠር መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ ያላቸውን የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አማራጮች በመጠቀም የመስኖ ልማቱን ለማድረስ ታስቦ የፓምፖቹ ድጋፍ መመቻቸታቸውን  ገልጸዋል።


 

በወጪ መጋራት መርህ የሶስቱ ወረዳዎች አርሶ አደሮች የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በማከናወን መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ከነገ ጀምሮ የፓምፖቹ  ተከላው እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

በአርሶ አደሮች የተዘጋጁ የውሃ ጉድጓዶች ጥልቀትና የውሃ መጠን  በመስፈርቱ መሰረት ስለመሆኑ በክልሉ ጂኢሎጂስቶችና በውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች በአግባቡ በማስጠናት መረጋገጡን አስረድተዋል።  

አንዱ በፀሐይ ኃይል የሚሰራው ፓምፕ አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት በአንድ ዙር የማልማት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ በፓምፖቹ በመጠቀም የተቀላጠፈ ልማት ውሰጥ በመግባት በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በፓምፖቹ አጠቃቀምና ጥገና ዙሪያ  ሥልጠና እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

የሰባት ዓመት መረሃ ግብር  የሆነው ተሳትፋዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም በክልሉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በተመደበ አንድ ቢሊዮን ብር የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው ወረዳዎች ከተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች መካከል 31 መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መካሄዱን አመላክተዋል።


 

የጉራጌ ዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት፤  ለማረቆ ወረዳ አርሶ አደሮች የተበረከቱት 15 ፓምፖች የግብርናውን ስራ ትርጉም ባለው መንገድ ለማዘመንና ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

በተለይ ወረዳው ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እያጋጠመ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለማቃለልና የአርሶ አደሩንም ህይወት ለማሻሻል እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ለላንፍሮና ሳንኩራ ወረዳዎች ድጋፍ የተደረጉትን  25 ፓምፖች  የተረከቡት የስልጤ ዞን  ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀያቱ ሙክታር በበኩላቸው፤  አሁን ላይ በመስኖ ልማት ረገድ ትልቅ ፈተና ሆኖ የተደቀነውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለማቃለል የፓምፖቹ እገዛ ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል።

በዞኑ በአነስተኛ ጉድጓድ ውሃ ሊለማ የሚችል ትልቅ አቅም እንዳለ ጠቅሰው ፤ፓምፖቹን ለዚሁ ስራ በማዋልና ለአርሶ አደሩ በቅርበት የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ውጤታማ ስራ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።


 

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ፤ውሃ አንዱ ከድህነት መውጫ መንገዳችን ነው ብለን እየሰራን ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻር የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል በፕሮግራሙ የገንዘብ ድጋፍ የቀረቡት የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን በምግብ ዋስትና ለታቀፉ አርሶ አደሮች ለማሰራጨት ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የመስኖ ልማት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ፕሮግራሙ በክልሉ  አነስተኛ መስኖ ተቋማትን በማስፋፋት አመርቂ ተግባር ማከናወኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም