ቀጥታ፡

ዋዛ ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስችል ስራ ተጀምሯል  - ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን 

አሶሳ መጋቢት 06 / 2015 (ኢዜአ)- የዋዛን ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ስራ መጀመሩን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት ዛሬ በተጀመረው ስድስተኛው የክልሉ የባህልና የዋዛ ፌስቲቫል መክፈቻ ስነ ስርአት ላይ ነው ። 

ባህል የሰው ልጆችን አኗኗር ከማሳየት ባለፈ እርስ በእርሳቸው በማስተሳሰር ለልማት ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን እንዳለው አቶ አሻድሊ ገልጸዋል። 

ይህንኑ መሰረት በማድረግ ዋዛ የትንፋሽ መሳሪያ በዩኔስኮ የማስመዝገብ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።

መሰል የባህል ፌስቲቫሎች የተፈጥሮ ሃብቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተተዋወቅ ለልማት ማዋል የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመው ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ባህላዊ እሴቶች አሁን ያለውን የክልሉን ሠላም ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የተናገሩት።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያው በሚቀርብባቸው መድረኮች የውጪ እና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ቀልብ ከሚስቡ የኢትዮጵያ ሃብቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያውን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህሎች በመላው ዓለም እንዲተዋወቁና እንዲለሙ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ነው አቶ ቀጄላ ያስረዱት።

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ተመራማሪ ዶክተር ዮናስ ይልማ በበኩላቸው  ዋዛን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥናቱ የሙዚቃ መሳሪያውን ባህላዊ እሴቶች፣ አሰራርና ተያያዥ ጉዳዮች ያካተተና በቅርቡ የሚጠናቀቅ መሆኑን ዶክተር ዮናስ አስታውቀዋል፡፡


 

ዋዛ የሚለው ቃል የአማርኛ አቻ ትርጓሜ “ጭፈራ” ማለት እንደሆነ ተመላክቷል።

ከቅሎች ቁርጥራጭ በቀርከሃና በባህላዊ ማጣበቂያ የሚሠራው ዋዛ የሙዚቃ መሳሪያ ከግማሽ እስከ ሶስት ሜትር ርዝመት ያለው እንደሆነም ተገልጿል።

ዋዛ የተለምዶ "ዙምባራ" የሚል መጠሪያ እንዳለው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም