ቀጥታ፡

የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የመልሶ ግንባታ ስራ የተጠናከረ ድጋፍ ያደርጋል--የዩኤን ዲ ፒ የኢትዮጵያ ተወካይ

አዲስ አበባ መጋቢት 06/2015(ኢዜአ):-የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የመልሶ ግንባታ ስራ የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ የድርጅቱ የልማት ፕሮግራም ኃላፊና የተመድ ቋሚ ተቀማጭ ተወካይ ቱርሃን ሳሊህ ተናገሩ።

የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ መንግስት ላቀደው የመልሶ ግንባታ ስራ የሁሉም ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤን ዲ ፒ) ኃላፊ ቱርሃነ ሳሊህ፤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቷ አካባቢ በነበረው ግጭት፤ በተፈጥሯዊ ችግሮች፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ድርቅ መፈተኗን አንስተዋል።

በእስካሁኑ ሂደት የነበሩ ፈተናዎችን ተቋቁማ ማለፏን አድንቀው በቀጣይም የሚያጋጥሙትን ሁሉ መሻገር እንደምትችል ፅኑ እምነት አለን ብለዋል።

የመንግሥትና የህዝቡ ተነሳሽነት ይህንኑ የሚያሳይ ነው ያሉት ቱርሃን ሳሊህ፤ የኢትዮጵያን የዘላቂ ሰላምና ልማት ጥረት ሁሉም አጋሮች ሊደግፉት ይገባል ነው ያሉት።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላምና ልማት ደጋፊ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በመንግስትና ህወሃት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ትግበራ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ የድርጅቱ ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሰላም ስምምነቱ የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለመልሶ ግንባታ ሂደቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በልማት ፕሮግራሙና ሌሎችም ድርጅቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምና ሌሎች ድርጅቶች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የስራ ፈጠራና ሌሎችም ተግባራት ላይ ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በግጭቱ በተጎዱ አካባቢዎች ከምናቀርበው የዕለት ደራሽ ሰብዊ እርዳታ ባሻገር ማህብረሰቡን በዘላቂነት የማቋቋም ሂደት ላይ የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም