በማንጎ ተክል ላይ በተከሰተ ተባይ ምክንያት ተገቢውን ምርት ማግኘት አልቻልንም---አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በማንጎ ተክል ላይ በተከሰተ ተባይ ምክንያት ተገቢውን ምርት ማግኘት አልቻልንም---አርሶ አደሮች
አርባ ምንጭ መጋቢት 6/2015 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን በማንጎ ተክል ላይ የተከሰተው ተባይ በምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ጠየቁ ።
የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ በበኩሉ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመፍትሄው እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በዞኑ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሻራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሴ ድልባቶ ለኢዜአ እንዳሉት የማንጎ ልማት በዋናነት ህይወታቸውን የሚመሩበት ነው።
የማንጎ ምርት ሽያጭ ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ቢሆንም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአካባቢያቸው በተከሰተ ተባይ በማንጎ ቅጠልና ፍሬ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በእዚህም ከማንጎ ምርት ተገቢውን ጥቅም እያገኙ ባለመሆኑ በኑሯቸው ላይ ጫና መፈጠሩን አርሶ አደሩ ተናግረዋል።
በዱቄት መልክ የተዘጋጀ ኬሚካል በማንጎ ተክሎች ላይ በመነስነስ እንዲሁም የተባይ ማጥመጃ ቁሶችን በማስቀመጥ እንዲሁም የተጠቁ የማንጎ ፍሬዎችን በመቅበር የተባዩን ስርጭት ለመግታት እየሞከሩ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
"ለልጆቻችን ቀለብ የምንሸምተው፣ የምናስተምረው እና የእርሻ በሬ የምንገዛው በማንጎ ምርት ሽያጭ ቢሆንም ተባይ ከተከሰተ ወዲህ ይህን ለማድረግ ተቸግረናል" ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዶርጋ ቀበሌ አርሶ አደር አስራት አዋሳ ናቸው።
ከዚህ ቀደም አካባቢው ከሙዝ ቀጥሎ በአብዛኛው በማንጎ ምርት የሚታወቅ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ በተባይ ምክንያት በማንጎ ምርት ላይ ጉዳት በመድረሱ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የሚመለከተው የመንግስት አካል ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሄ በማምጣት ከችግራቸው እንዲታደጓቸው ጠይቀዋል።
የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ቲቆ ትላንቴ በበኩላቸው "ነጭ ስኬል" የተሰኘ የማንጎ ተባይ ላለፉት ሦስት ዓመታት በአካባቢው ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም በተለይ በዞኑ 10 የማንጎ አምራች ወረዳዎች ከ5ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የማንጎ ማሳ ላይ ተባዩ መከሰቱን ገልጸዋል።
"ማንጎ በዞኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው የፍራፍሬ ተክል ነው" ያሉት አቶ ቲቆ ትላንቴ፣ ከአካባቢ ገበያ አልፎ ለማዕከላዊ ገበያ ሲቀርብ የነበረው የማንጎ ምርት ጉዳት ስለደረሰበት አምራቹ ለችግር መጋለጡን ተናግረዋል።
አምራቹ ዘወትር ለማሳው ክትትል እንዲያደርግና የማሳውን ንጽህና እንዲጠብቅ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በኬሚካል ርጭት ችግሩን በጊዜያዊነት ለመቆጣጠር በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተባዩን በዘላቂነት ለማጥፋት ከአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ከአርባ ምንጭ እጽዋት ክሊኒክ ጋር በመቀናጀት ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማንጎ "ነጭ ስኬል" ተባይ የማንጎ ምርትን ከመቀነስ ባለፈ ሙሉ በሙሉ ዝርያውን የማጥፋት አቅም ያለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ተወካይና የሰብል ተመራማሪው አቶ መለሰ ለማ ናቸው።
ተመራማሪው እንዳሉት ተባዩ ማንጎን ብቻ ሳይሆን ከ50 በላይ የፍራፍሬ ተክሎችን የማጥቃት አቅም አለው።
በተቀናጀ የተባይ መከላከያ ዘዴ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን ፕሮጀክት ተቀርጾ ለመፍትሄው እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ በጣም የተቀራረቡ የማንጎ ቅርንጫፎችን በማሳሳት በውስጣቸው አየር በአግባቡ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።
"ከእዚህ ጎን ለጎን ስፓርክ 250 የተሰኘ ኬሚካል በመጠቀም የተባዩን ስርጭት ለመቀነስ የምርምር ማዕከሉ የበኩሉን እየተወጣ ነው" ብለዋል።