ኢትዮጵያ ፊፋ በእግር ኳስ ልማት ፕሮግራም በሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፊፋ በእግር ኳስ ልማት ፕሮግራም በሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ መጋቢት 06/2015 (ኢዜአ)፦ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር /ፊፋ/ በእግር ኳስ ልማት ፕሮግራም በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
ፊፋ በሥሩ ያቀፋቸው አባል ሀገራት በወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በታዳጊዎች አቅም ማጎልበቻ ላይ ለሚሰሩት ተግባራትና ሌሎች አጠቃላይ የእግር ኳስ ልማት ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሀገራት እግር ኳሳቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ተከትሎ በሚያቀርቡት አሳማኝ የልማት ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ተጨማሪ ድጋፎችን ይሰጣል።
ይህን ድጋፍ የሚጠይቁ ሀገራት ደግሞ ሊያሟሏቸው የሚገቡ መመዘኛ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን ከመስፈርቱ በተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ የሥራ መርሃ-ግብር ወይም ፕሮፖዛል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም አኳያ ችግሮች ይታይባት እንደነበር ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፊፋ "ፎርዋርድ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም" በሚል ከሚሰጠው ድጋፍ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራት በፌዴሬሽኑ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከዚህ በፊት ከፊፋ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ፌዴሬሽኑ የራሱን የህንፃ ግዥ መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይ ፊፋ አባል ሀገራት ለሚያከናውኗቸው መሰረታዊ የእግር ኳስ ልማት ሥራዎች ከሚሰጠው ድጋፍ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን በተሰጠው ሥልጠና ኢትዮጵያ መካፈሏን በማስታወስ ይህን ተከትሎ በእግር ኳስ ልማት ላይ የሚሰሩ ተግባራትን በመለየት እስከ ሰኔ ወር ድረስ ለፊፋ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ፊፋ ለእግር ኳስ ልማት በሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ ለመሥራት የታሰቡ ፕሮጀክቶች እንዳሉና ከእነዚህ መካከል ሁለገብ የስፖርት ማዕከል የመገንባት ፍላጎት ቀዳሚው መሆኑን ነው የገለጹት።
ሁለገብ የስፖርት ማዕከል በውስጡ የተጨዋቾች ሕክምናና ማገገሚያ፣ ቤተ-ሙከራና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ነው ብለዋል።
ይህን የስፖርት ማዕከል አያት አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህቀት አካዳሚ ግቢ ውስጥ ለመገንባት ዕቅድ እንደተያዘም ነው የገለጹት።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በቋሚነት ልምምድ የሚሰራበት ቦታ እንዲኖረው ለማድረግና በሴቶች እግር ኳስ ልማት ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት መታቀዱንም ተናግረዋል።
ይህንኑ ሃሳብ እውን በማድረግ " ከፊፋ ፎርዋርድ ፕሮግራም" ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችለውንና ለፊፋ የሚላከውን ፕሮፖዛል የማዘጋጀት ሥራ በፌዴሬሽኑ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
እግር ኳስን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ለአሰልጣኞች ሥልጠና ስትሰጥ የቆየችው ከፊፋ በተወሰዱ የሥልጠና መመሪያዎች መሆኑን በክፍተት አንስተዋል፡፡
የሥልጠና መመሪያው የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገቡ መሆናቸውን በማስታወስ፤ አሁን ላይ የሀገሪቱን እግር ኳስ ታሳቢ ያደረገ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።