ቀጥታ፡

ባለፉት 2 ሳምንታት ብቻ በቦረናና ሞያሌ አካባቢ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 28 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ ነክ ድጋፍ ተደርጓል--- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ባለፉት 2 ሳምንታት ብቻ በቦረና እና ሞያሌ አካባቢ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 28 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ ነክ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።

ማኅበሩ በቦረናና ሞያሌ አካባቢ በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

በአካባቢው በተለያየ ጊዜ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት የሚፈታ ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚገባም አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ በመግለጫው የማኅበሩ ቡድን ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመስክ ምልከታ ማድረጉን ገልጸው መንግሥት ለተጎጂዎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተመልክተናል ብለዋል።

ከመንግሥት ጎን ለጎንም የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ አንደሚገኙ አብራርተው በድርቁ ተጎጂ የሆኑ ወገኖች በአርብቶ አደርና ግብርና ስራዎች የተሠማሩ በመሆናቸው ይህንን ያማከለ ድጋፍ ከሁሉም ወገን እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በአካባቢው በተለያየ ጊዜ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት የሚፈታ ስትራቴጂ በመንግሥትና አጋር አካላት መንደፍ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ የሚገኘውን ድጋፍም በመንግሥት መሪነት በአንድ ቋት በማስተዳደር ተደራሽ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።


 

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ጌታቸው ታአ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት አመታት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

ማኅበሩ እ.አ.አ በ2022 በደቡብ ክልል ከንባታ ጠንባሮና ጋሞ ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና፣ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ እና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች፣ በሶማሌ ክልል ሸበሌ፣ ፋፈን እና አፍዴር ዞኖች ለ14 ሺህ 530 አባዎራዎች/እማዎራዎች ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።

ማኅበሩ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በቦረናና በሞያሌ አካባቢ ለሚገኙ ወገኖች ብር 28 ሚሊዮን የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ ለ6ሺህ 130 ሰዎች (1226 አባዎራዎች) እንዲሁም ለ200 አባዎራዎች 800ሺህ ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ተጨማሪ ድጋፎችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ማኅበሩ ቀጣይነት ያለው የሀብት ማሰባሰብ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

በዘመቻውም ወደ 10 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶ እስካሁን ወደ 8 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ገቢ ሆኗል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት ጋርም በመተባበር እየተካሄደ ባለው የአይነትና የጥሬ ገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ በጥሬ ገንዘብ ወደ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በአይነት ወደ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ተቋማትና ግለሰቦች 4 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አቶ ጌታቸው አንስተው በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡

የተለያዩ ወገኖችና ተቋማት በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም