ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ስኬት እውን ለማድረግ የጋራ ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

 አዲስ አበባ መጋቢት 06/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ስኬት እውን ለማድረግ የጋራ ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና እና እውቅና ሰቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በትብብር እያካሄድናቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ክንውኖች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገበባቸው ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ስኬት እውን ለማድረግ በቀጣይም የጋራ ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።


 

ኢትዮጵያዊያን ስንተባበር የማናሳካቸው የልማት እቅዶችና የማንሻገራቸው ችግሮች የሉም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና እድገት የጋራ ጥረታቸው መጠናከር አለበት ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በአዲስ አበባ ለተካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማ ክንውን አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ እንዲሁም በቱርኪዬ ተከስቶ በነበረው ርእደ መሬት የነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተው ለተመለሱ ኢትዮጵያዊያን ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ በመሪዎች ጉባኤ ላይ በዘገባ ለተሳተፉት ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የህብረቱ ጉባኤ በስኬት የተጠናቀቀው በርካቶች በቅንጅትና በመተባበር በሰሩት ስራ መሆኑን አስታውሰው ይሄው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያን መፃኢ እድል የተሻለ ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ በተለይም በሚዲያ ዘርፍ ሁነቱን ለህዝቡ ለማድረስ ለሰሩ የሚዲያ ተቋማት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም