ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ቁርጠኛ አቋም አላት- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ቁርጠኛ አቋም አላት- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ መጋቢት 5/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳይ ምክትል ዋና ጸሐፊ ኤነሪኬ ሞያ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ሕብረት የጋራ ጥቅሞች በሆኑ የሁለትዮሽ እና የባለዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለኤነሪኬ ሞያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ እያደረጋቸው በሚገኙ ጥረቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ሚናም ገለጻ አድርገዋል።
በሌላ በኩል አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳይ ምክትል ዋና ጸሐፊ ኤነሪኬ ሞያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አጠቃላይ የትግበራ ሰነድ ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲሁም ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆንና በሽግግር ፍትሕ ስርዓት እያከናወነች ያለችውን ጥረቶች አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለቀጣናው ሰላም መሆን አስፈላጊ መሆኑንም ምክትል ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልግ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።