ቀጥታ፡

የኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ ህግ "ሄር ኢሴ " በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ድሬዳዋ መጋቢት 5 /2015(ኢዜአ)፡- የዘላቂ ሰላም ማስጠበቂያና የማንነቱ መገለጫው እንደሆነ የሚነገረው  የኢሳ ማህበረሰብ  ባህላዊ ህግ "ሄር ኢሴ " በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁ  ተገለጸ። 

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አመራሮች በሰነዱ ዝግጅት ዙሪያ ከኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ አባቶችና ከማህበረሰቡ ተወካዮች ጋር  ዛሬ በድሬዳዋ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደተናገሩት ፤ በምስራቁ የኢትዮጵያ  ክፍል ከሚገኙ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የኢሳ ማህበረሰብ ያልተፃፈ መተዳደሪያ ህግ " ሄር ኢሴ" አንዱ ነው።

የኢሳ ማህበረሰብ ማንነት መገለጫ እንደሆነ የሚነገረው  " ሄር ኢሴ" በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለሀገር ገፅታ ግንባታና ለቱሪዝም ሃብት ዕድገት አስተዋጽኦ  እንደሚኖረው  ተናግረዋል።

ቅርሱን  በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

ከሶስት ሳምንታት በኋላ ቅርሱን ለማስመዝገብ የተዘጋጀው የማስመረጫ ሰነድ ለዩኔስኮ ከመቅረቡ በፊት የማህበረሰቡ የ"ገንዴ" አባቶችና ሽማግሌዎች ተወያይተውበት እንዲያዳብሩ ተደርጓል ብለዋል።

ቅርሱ የህዝብ ለህዝብ  ባህላዊ  ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትም  ገልጸዋል ።

ውይይቱን የመሩት የማህበረሰቡ አባል  አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በበኩላቸው ፤ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን በሀገራችን  የምንኮራባቸውን የማንነት መገለጫ የሆኑትን ባህላዊ ሃብቶችና ጥበቦች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

"ሄር ኢሴ "የኢሳ ማህበረሰብ መገለጫውና የዘላቂ ሰላሙ ማስጠበቂያ ባህላዊ እሴቱ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤  ይህ ቅርስ ማህበረሰቡ በእኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያስተዳድርበት ያልተፃፈ ባህላዊ ህግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም  ባሻገር የስነ ፈለግ፣የስነ ዕፅዋት ፣ የእንስሳት እርባታና የእርሻ ጉዳዮችን ጨምሮ ለትውልድ የሚጠቅሙ ሌሎችም ጥበቦችና  ትውፊቶች ባለቤት መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን  ባህላዊ ሃብቶች ፣ ጥበቦችና ዕውቀቶች ጥቅም ላይ እንዲውል ትኩረት በመስጠት ዘላቂ ሰላም ፣ልማትና ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት እንዲያግዙ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል ።

በሶማሌ ክልል የሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ ሃብቶችን ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ  ልማትና ለቱሪዝም ዕድገት እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወርሰን አወል ገልጸዋል።


 

"ሄር ኢሴ"ን በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተገባደደ የሚገኘው ስራ በሌሎች ባህላዊ ሃብቶች ላይ ይበልጥ እንዲሰራ የሚያነሳሳ መሆኑንም አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ አባቶችና የማህበረሰቡ ተወካዮች  ቅርሱን በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የመስቀል፣የጥምቀት ፣የገዳ ስርዓትና ፊቼ ጨምበላላ ባህላዊ ሃብቶቿን በማይዳሰሱ ቅርስነት በዩኔስኮ ማስመዝገቧን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም