ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ 

ባህር ዳር መጋቢት 05 /2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለሁሉም ደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ከቁልፍ ደንበኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ባካሄደበት ወቅት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአማራ ክልል ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰሎሞን ጣሰው እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

መንግስት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ካለፉት 12 ዓመታት ጀምሮ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ተደራሽነት ፕሮግራም 1 ሺ 936 የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በተለያየ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ እየሄደ ባይሆንም ቀደም ሲል ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት በክልሉ 2 አነስተኛ የሶላር ማከፋፈያዎችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ሁለት ቀበሌዎችን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

ዘንድሮም ተጨማሪ 6 ቀበሌዎችና አነስተኛ ከተሞችን የሶላር መብራት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከኃይል ማሰራጫ መስመሮች እርጅናና አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር ለመፍታትም የማሰራጫ መሰረተ ልማቶችን አቅም የማሳደግ፣ የማደስና የመቀየር ስራዎችም እየተሰሩ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በክልሉ አሁን ያሉትን 725 ሺህ የተቋሙ ቀጥተኛ ደንበኞችን ቁጥር በቀጣይ ሁለት ዓመታት ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለማድረስ መሰረተ ልማት የማደስና የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኤሌክትሪክ ዝርፊያና መሰረተ ልማት ስርቆት የተነሳ የሚያጋጥመውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ለመፍታት በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካል መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በክልሉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በኃይል አቅርቦት እጥረት ስራ ያልጀመሩ እንዳሉ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ደሴ አሰሜ በበኩላቸው፤ ክልሉ ያለበትን የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ተጨማሪ አዳዲስ ሰብስቴንሽኖች መገንባትና ያረጁ መስመሮችን መጠገን ይኖርበታል ብለዋል። 

ቀደም ሲል የነበሩ የኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ከለውጥ በኋላ ችግሩን ለማስተካከልና ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በተደረጉ ጥረቶች መሻሻል እየታየ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የሚደርሰውን ዘረፋ ለማስቆም የፀጥታ አካላትና ህብረተሰቡ በጋራ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የኤምኤስኤ ቢዝነስ ግሩፕ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አበረ አበራ በበኩላቸው ባህር ዳር ላይ ለተቋቋሙ ፋብሪካዎች መንግስት ቀጥታ ከሰብስቴሽን የኃይል አቅርቦት እንድናገኝ አድርጓል ብለዋል። 

በዚህም የሲሚንቶ ማሸጊያ ቀረጢትና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሃይል መቆራረጥ ሳያጋጥማቸው በሙሉ አቅማቸው መስራች የሚያስችል ሁኔታ እንደተፈጠረ ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ የተቋሙ ደንበኞች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም