ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ማድረግ ከቀድሞ በተሻለ  ችግር ፈቺ  እንዲሆኑ ያስችላል -  ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ 

ሐረር ፤ መጋቢት 5 /2015 (ኢዜአ) ፡ - ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ማድረግ ከቀድሞ በተሻለ  ችግር ፈቺ   እንዲሆኑ  ለማስቻል  ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንደሚኖራቸው   የትምህርት ሚኒስትር  ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ። 

ሚነስትሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ለማድረግ በተዘጋጀ መነሻ ፅሁፍ ላይ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  ምሁራን ጋር በመከሩበት ወቅት፤  እውነትና እውቀትን የሚፈልግ ተቋም በነፃነት ማሰብ የሚችሉ ምሁራን ሊኖሩት ይገባል  ብለዋል፡፡

ለዚህም  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተፅዕኖ ወጥተው ራስ ገዝ በመሆን  እራሳቸውን በራሳቸው  እንዲያስተዳድሩ ለማስቻል በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን ከቀድሞ በተሻለ  አቅማቸውን በማሳደግና  የሚካሄድባቸው ምርምሮች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው  ሚኒስትሩ  ገልጸዋል፡፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲም  ራስ ገዝ በማድረጉ ሂደት እራሱን በመፈተሸ  ሀገርን በሚጠቅሙ ችግር ፈቺ  ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡


 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ በበኩላቸው፤  ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ገበያ የሚፈልገውን የትምህርት ዘርፍ በራሳቸው አጥንተው በመወሰን  እንዲያስተምሩ እድሉን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲዎቹ በውስጥ አቅም የሚያመነጩትን ገቢ በመጠቀም ያዋጣኛል የሚሉትን የሰው ሃይል በገበያ ዋጋ ቀጥረው በማሰራት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘገቡ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ገበያ የሚፈልገውን ሃይል ለማምረት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ  ነው ዶክተር ጀማል የገለጹት።


 

በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ህትመቶች ባለሙያና መምህር  ቅድስና ሰብስቤ በሰጡት አስተያየት፤  ዩኒቨርሲቲዎቹ ራስ ገዝ መሆናቸው በራስ የመወሰን አቅማቸውን  እንደሚያጎለብትላቸውም ተናግረዋል።

 ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ ራሳቸውን እንዲችሉ አስፈላጊውን መሰረተ ልማቶች ለማሟላት ከወትሮው  በተለየ መልኩ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። 

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት  ደግሞ የዩኒቨርሲቲው እንስሳትና የተፈጥሮ ግጦሽ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጥበቡ ማናዬ ናቸው። 

የተሻለ ትምህርት ቤትንና ተማሪን  ለመፍጠር ዩኒቨርሲቲዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እራስን ማስተዳደር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በጥናትና ምርምር ውጤቶች የሚገኙ ገቢዎችን ዩኒቨርሲቲውን ብሎም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ፕሮግራሙ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ተስፋ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎችን እሳራቸውን በማስቻሉ ሂደት ያሉባቸውን ክፍተቶችን ለመሙላት መንግስት  ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሐረሚያ ዩኒቨርሲቲ   ራስ ገዝ ከሚሆኑ ስምንት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ  መሆኑ ተገልጿል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም