ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ ለተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች 355 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ግብዓቶች ተደራሽ ሆነዋል

አዲስ አበባ መጋቢት 05/2015(ኢዜአ)፦ በ2015 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ለተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች 355 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ግብዓቶች ተደራሽ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ገለጸ።

የድርጅቱ የግብዓት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ንጉሴ ገብረማሪያም፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ2015 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የተጠናከረ የግብዓት አቅርቦት መከናወኑን ገልጸዋል። 

በተለይም ለጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ የግብርና ማቀነባበሪያ፣ ለግንባታ እና የኬሚካል ግብዓት ኢንዱስትሪዎች ሰፊ ግብዓት ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ 355 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ለአምራቾች እንዲደርሱ መደረጉን አቶ ንጉሴ ገልጸዋል።

ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች የቆዳ ማከሚያ ግብዓት በየወሩ ከ52 ሺህ ኩንታል በላይ ጨው በቋሚነት እያቀረበ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከውጭ የሚገባውን የኬሚካል እጥረት ለማቃለልም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንደሮው በጀት ዓመት በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተለያዩ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የመንግስት የልማት ድርጅት ሲሆን ከተቋቋመበት አላማ መካከል አንዱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም