ቀጥታ፡

በመጪዎቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን በስፋት የሚያዳርስ የዝናብ ስርጭት ይኖራል

አዲስ አበባ መጋቢት 05/2015 (ኢዜአ)፦ በመጪዎቹ 10 ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ከስተቶች አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚኖራቸውና የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን በስፋት የሚያዳርስ የዝናብ ስርጭትና መጠን እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው በመጪዎቹ 10 ቀናት የሰሜን ምስራቅ፣የምስራቅ፣ የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች በመጠንም ሆነ በስርጭት የተስፋፋና የተጠናከረ ዝናብ ያገኛሉ፡፡

የዝናብ ስርጭቱ በተለይም ወደ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ እንደሚሄድ የአየር ትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በጥቂት ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎቹን ዋቢ በማድረግ  አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ በመጪዎቹ አስር ቀናት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣ ጅማ፣ኢሊአባቦራ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣አርሲና ባሌ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ መካከለኛ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

በጥቂት ቦታዎች በተለይም ደቡብ አፋር፣ ምስራቅ ሸዋ እና የደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ። 

የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ተብሏል። 

በሌላ በኩል በምዕራብ አማራ፤ ጋምቤላ እና በደቡባዊ ሶማሌ ክልል የሀገሪቱ ቆላማ ሥፍራዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35 ድግሪ ሴልሽየስ በላይ መጠን እንደሚኖረው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የእርጥበት ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ተመላክቷል፡፡ 

ይህ ሁኔታ በተለይም ለበልግ አብቃይ አካባቢዎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግ እና የተለያዩ የበልግ ሰብሎችን ለማልማት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም አስቀድመው ለተዘሩ የበልግ ወቅት ሰብሎችም ሆነ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ሚና እንደሚኖረውም እንዲሁ፡፡

በተጠቀሱት ቀናት የሚኖረው የአየር ትንበያ አብዛኛውን የበልግ እርጥበት ተጠቃሚ ተፋሰሶች የሚሸፍን ይሆናል።

በመሆኑም አብዛኛው ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አዋሽ፣ ገናሌ ዳዋ፣ የላይኛው እና መካከለኛ ዋቤ ሸበሌ፣ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣ ተከዜ እና አባይ ተፋሰሶች ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ እርጥበት ያገኛሉ።

ይህም ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን የገጸ ምድር የውሃ መጠንን ሊያሻሽል እንደሚችል ይጠበቃል።

በሌላ በኩል በአፋር ደናክል፣ በታችኛው ዋቤ ሸበሌ፣ ገናሌ ዳዋ እና ኦጋዴን መጠነኛ እርጥበት የሚያገኙ ሲሆን፤ የተቀሩት ተፋሰሶች ደረቅ እና ከፊል ደረቃማ ሁኔታ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም