የአርኪዎሎጂና ኃይማኖታዊ ቅርሶችን ከህገ-ወጥ ዝውውር ለመጠበቅ ህብረተሰቡና የፍትህ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአርኪዎሎጂና ኃይማኖታዊ ቅርሶችን ከህገ-ወጥ ዝውውር ለመጠበቅ ህብረተሰቡና የፍትህ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ መጋቢት 5/2015(ኢዜአ): በኢትዮጵያ ለህገ ወጥ ዝውውር እየተጋለጡ ያሉ የአርኪዎሎጂና ኃይማኖታዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ ህብረተሰቡ፣ የፍትህ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውር መከላከልን በተመለከተ ለፍትህ አካላት፣ የሃይማኖት ተቋማት የጉምሩክና ባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኃይማኖታዊና የአርኪዎሎጂ ቅርሶች በባህላዊ ስጦታ እቃዎች ስም ላልተገባ ተግባርና ዝርፊያ እየተጋለጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅርሶቹ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከመዘረፋቸው በተጨማሪ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
ይሁን እንጂ ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከባለስልጣኑ በተጨማሪ የህብረተሰቡ፣ የፍትህ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ በመሆኑ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በሌሎች የፍተሻ ጣቢያዎች የሚሰሩ የፍተሻ ባለሙያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው በበኩላቸው ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውር የባህል፣ የማንነት እሴትና የታሪክ ዘረፋ በመሆኑ የፍትህ አካላት፣ የእምነት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አካላት ወንጀሉን በመከላከል የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡