በኩታ ገጠም የመስኖ ስንዴ ልማት ከራሳችን አልፎ ለገበያ ምርታችንን እያቀረብን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኩታ ገጠም የመስኖ ስንዴ ልማት ከራሳችን አልፎ ለገበያ ምርታችንን እያቀረብን ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 5/2015(ኢዜአ):- በኩታ ገጠም የመስኖ ስንዴ ልማት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ ምርታቸውን እያቀረቡ መሆኑን የምስራቅ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በዞኑ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ በተያዘው የበጋ ወቅት 1 ነጥብ 33 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኖ፤ 52 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንደ ሀገር ከድህነት ለመውጣት የሚደረግ የጋራ ርብርብ በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ስንዴን በመስኖ እያለሙ ካሉ አካባቢዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ተጠቃሽ ነው፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን አርሶ ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ተሾመ ታደሰ ፣ አቶ አብዮት ረጋሳ ና አቶ ዋቄ ዶዮ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት በሁሉም ወቅቶች ስንዴ ማምረት ጀምረዋል፡፡
መንግስት በሚያቀርበው ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም የውሃ መሳቢያ ፓምፖች አማካኝነት የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት በየጊዜው ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በቴክኖሎጂ የታገዘ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በመተግበር ምርታማነታቸውን በመሻሻሉ አርሶ አደሮቹ ከምግብ ፍጆታቸው አልፎ ምርታቸውን ለገበያ ማቅርብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው በዞኑ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በ65 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በለማ የበጋ መስኖ ስንዴ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውሰው፤ በዘንድሮው ዓመት 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ይህም እቅድ ለማሳካት የሚያስችል የተለያዩ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ መቅረቡንም ተናግረዋል።
አካባቢው የአዋሽ ወንዝ የሚያልፍበት እንዲሁም ከርሰ ምድርና ገጸ- ምድር ውሃ ሃብት ያለው በመሆኑ ይህንን ሃብት ለመስኖ ልማት ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባን የስንዴ ምርት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ከመሸፈን ባሻገር በዘንድሮው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የስንዴ ምርት ለወጪ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ ይታወቃል፡፡