ከምስራቅ አፍሪካ ለስራ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት የሚሄዱ ዜጎችን መብት ማስከበር አላማ ያደረገ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ከምስራቅ አፍሪካ ለስራ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት የሚሄዱ ዜጎችን መብት ማስከበር አላማ ያደረገ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ)፦ ከምስራቅ አፍሪካ ለስራ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት የሚሄዱ ዜጎችን መብት ማስከበር አላማ ያደረገ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተጠቆመ።
አራተኛው ቀጣናዊ የሚኒስትሮች የፍልሰት ጉባኤ በሙያተኞች ደረጃ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
የቀጣናዊ የሚኒስትሮች የፍልሰት የቴክኒካል ኮሚቴ ሊቀ-መንበር እና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አሰግድ ጌታቸው ከፍልሰት ጋር በተያያዘ የቀጣናው አገራት ያላቸው ትብብር እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከምስራቅ አፍሪካ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት ለስራ የሚሄዱ ዜጎችን መብትና ጥቅም በትብብር ለማስከበር የሚያስችሉ "በርካታ ስራዎች" እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከደሞዝ፣ የዓመት እረፍት እና የስራ ላይ ደህንነት ጋር ተያይዞ ዜጎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በትብብር መፍታት የሚያስችሉ አሰራሮች መቀረጻቸውን አመልክተዋል።
ለዚህም በቴክኒካል ኮሚቴው በሚገኙ የባለሙያዎች ቡድን የተዘጋጀው ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው አቶ አሰግድ የጠቆሙት።
የአካባቢው አባል አገራት የሰራተኛ አታቼ በሌለባቸው የዓለም አገራት የሰራተኞችን መብት ለማስጠበቅ በትብብር መሥራት የሚያስችል ሰነድ በጉባኤው ላይ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል "ኢትዮጵያ ሕገወጥ የሰዎች ስደትን ለመከላከል በአገር ውስጥ የሚፈጠረውን የስራ እድል ለማስፋት እየተሰራ ነው" ሲሉ የኮሚቴው ሊቀ መንበር የገለጹት።
ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በሕጋዊ መንገድ ሄደው ለመስራት ለሚፈልጉ ዜጎችን ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
ዜጎች በመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ዜጎች ሄደው መስራት እንዲችሉ የሁለትዮሸ ስምምነቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ ጂያን ዣኦ ጉባኤው በፍልሰት ዙሪያ ስራዎችን በትብብር ለማከናወን ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ፍልሰትን መከላከል የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ ድርጅቱ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአራተኛው ቀጣናዊ የፍልሰት ጉባኤ 11 የአካባቢው አባል አገራት የተውጣጡ የዘርፉ ሙያተኞች ተወካዮች እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን ዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶችና የልምድ ልውውጥ ይደረጋል ተብሏል።
ጉባኤው ለቀጣይ አራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ሙያተኞች በስራ ፈጠራ፣ በስደት ተመላሾችና በሌሎች የተወያዩባቸው ጉዳዮችን ለሚኒስትሮች በማቅረብ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሶስተኛው ቀጣናዊ የሚኒስትሮች የፍልሰት ጉባኤ እ.አ.አ ሚያዚያ 2022 በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ፎረም ሊቀ-መንበርነቱን ከኬንያ መረከቧ ይታወቃል።