ከዓመታት በኋላ የያቤሎ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችን ተስፋ ያለመለመ ዝናብ መዝነቡ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ከዓመታት በኋላ የያቤሎ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችን ተስፋ ያለመለመ ዝናብ መዝነቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2015(ኢዜአ)፦ ከዓመታት በኋላ የያቤሎ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችን ተስፋ ያለመለመ ዝናብ መዝነቡ ተገለጸ።
በምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ሳቢያ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ነው።
ከእነዚህ አካባቢዎች አንዱ የሆነው በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ቦረና ዞን ዝናብ ካገኘ ተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች አልፈዋል።
በዚህ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያም በእንስሳት ሃብት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይም መልከ ብዙ ቀውሶች ተጋርጠው ቆይተዋል፡፡
መንግስት ድርቁ ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ ተጎጂዎችን ለመታደግ የአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎች እና ዘላቂነት ያላቸው የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡
የቦረና እና አካባቢው ዝናብ የሚያገኘው በበልግ ወቅት በመሆኑ ለዓመታት ዝናብ የናፈቃቸው አርብቶ አደሮች ይህን ጊዜ ተስፋ ሰንቀው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዝናብ አጠር በሆኑና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ዝናብ የሚያስከትሉ የደመና ክምችቶች መታየታቸውን ለኢዜአ መግለጹ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በያቤሎ እና አካባቢው ትናንት ከሰዓት ዝናብ ጥሏል።
በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተርም የያቤሎ ከተማ ነዋሪዎቹ ዝናብ በመዝነቡ ደስታቸውን ሲገልጹ አስተውሏል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች "ከዓመታት የራቀን ዝናብ በመመለሱ ተደስተናል፤ ለነገ ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎናል" ብለዋል።
ነዋሪዎቹም ዕለቱን 'የደስታና ምስጋና' ቀን ሲሉት ተደምጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ላለውን ጥረት አመስግነዋል።
በቦረና ዞን በድርቅ ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ከ867ሺህ በላይ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው።