ቀጥታ፡

ሊጉ ወጣት አመራሮችን ለማፍራት እስከታች ባለው መዋቅር ሪፎርም እንደሚያካሂድ አስታወቀ

ባህር ዳር መጋቢት 4 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ተተኪ ወጣት አመራሮችን ለማፍራት እስከ ታችኛው ድረስ ባለው መዋቅር ሪፎርም እንደሚያካሂድ አስታወቀ። 

ሊጉ "በወጣቶች አቅም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ይረጋገጣል!" በሚል መሪ ሃሳብ የስልጠና መድረክ  በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው። 

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የሊጉ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ እንደተናገረው፤ ሊጉ በሀገሪቱ በሚገኙ 1ሺህ 100 ወረዳዎች መዋቅሩን ዘርግቶ ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት እየሰራ ይገኛል።

በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክፍተቶች ለይቶ በየደረጃው በማስተካከል ሀገር ለማሻገር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።

ሆኖም የሊጉ መዋቅር እስካሁን በተሄደበት መንገድ ሊቀጥል እንደማይችል መገምገሙን ያመለከቱት ወጣት አክሊሉ፤ ከመሪ ድርጅቱ ጋር በመሆን ከስልጠናው በኋላ እስከ ታችኛው ድረስ ባለው መዋቅር ሪፎርም እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ሊጉ በሪፎርሙ ጠንካራና የላቀ እውቀት ያላቸውን ወጣቶችን በማወዳደር ጭምር ወደ ሊጉ አመራርነት እንዲመጡ የሚያደርግ አሰራር እንደሚዘረጋም አመልክቷል።

በስልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙት የሊጉ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ፓርቲው የተረከባትን ሀገር አንድነቷ ተጠብቆና በሁለንተናዊ እድገቷ ተምሳሌት ሆና እንድትቀጥል ለሪፎርሙ ስኬት ተግተው እንዲሰሩ አሳስቧል።

ስልጠናው በፓርቲው አቋምና አካሄዶች ላይ ግልጽነት መፍጠር፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታውን ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ መተንተንና ማወቅ፣ ትስስርን ማጠናከርና ኅብረ ብሄራዊነት ውበት መሆኑን ለመረዳት እንደሚያስችል ተናግሯል።

የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ በበኩላቸው፤ የወጣቶችን የመሪነት ሚና ለማሳደግ በተደረገ ጥረት አሁን ላይ 27 በመቶ የክልሉ አመራሮች ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሄንን መልካም እድል በማስቀጠል ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ማማ ለማሻገር የህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወጣቱን አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲው እንደሚያምን ተናግረዋል።

ስልጠናው ብልጽግና የነገ ፓርቲ ነው የሚለው መርህ የበለጠ መሬት እንዲነካ የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት  ዶክተር ጋሻው፤ ዓበይት ግቦች እንዳሉትም ጠቅሰዋል።

በዚህም ከላይ እስከ ታች ያለውን የሊጉ አደረጃጀት ጠንካራና ለሀገር አለኝታ በማድረግ በየጊዜው የሚገጥሙ ተግዳሮቶች በወጣቱ የነቃ ተሳትፎ በመፍታት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በየደረጃው ወደሚገኘው የሊጉ አመራር ቦታ የሚመጡ ወጣቶች የተማሩ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ለሀገር አንድነትና ለህዝብ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት የሚታገሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ከሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም