የኢትዮጵያና የቻይናን ግንኙነት ለማጠናከር የቻይና መንግስት በትኩረት ይሰራል…በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል

484

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የቻይና መንግስት አዲስ ከተመደቡት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ሆንግ ሊ ገለጹ።

ዳይሬክተር ጀነራሉ ይህን ያሉት በቻይና አዲስ የተሾሙት አምባሳደር ተፈራ ደርበው የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጅ ለቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው።


 

ዳይሬክተር ጀነራሉ ለአምባሳደሩ በአዲሱ ሹመታቸው የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቻይና እና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የቻይና መንግስት ከአዲሱ አምባሳደር ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውም ዳይሬክተር ጀነራሉ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ተፈራ በበኩላቸው ዳይሬክተር ጀነራሉ የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ከዚህ ቀደም ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።


 

አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ለዳይሬክተር ጀነራሉ ካስረከቡ በኋላ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዎ ፔንግ ጋር በስልክ ተገናኝተዋል።

ዳይሬክተር ጀነራሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪን ጋንግ በጥር ወር በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስታውሰው የጉብኝቱን አስፈላጊነትም ጠቅሰዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጥሩ የሚባል ግንኙነት አዲስ በተሾሙት አምባሳደር የሹመት ዘመንም እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም፤ ለሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅም ከአዲሱ አምባሳደር ጋር ለመስራት በቻይና መንግስት በኩል ያለውን ፍላጎት አስታውቀዋል።

አምባሳደር ተፈራ በበኩላቸው ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም