ኢትዮጵያ በ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በብስክሌት ስፖርት ለመሳተፍ የሚያስችላትን ውጤት ለማግኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው- የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በብስክሌት ስፖርት ለመሳተፍ የሚያስችላትን ውጤት ለማግኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው- የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በብስክሌት ስፖርት ለመሳተፍ የሚያስችላትን ውጤት ለማግኘት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የብስክሌት ስፖርተኞች ውጤት ለማምጣት በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እየተሳተፉ መሆኑንም ገልጿል።
የኦሊምፒክ ጨዋታ በዓለም ትልቁ የስፖርት መድረክ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው እ.አ.አ 1956 በሜልቦርን በተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነው።
ኢትዮጵያ በወቅቱ በአትሌቲክስ እና ብስክሌት ስፖርት እንደተሳተፈች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ያደረገችውን 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጨምሮ ለሰባት ጊዜ በውድድሩ ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
ይሁንና ኢትዮጵያ በእ.አ.አ 1992 በባርሴሎና ከተማ በተካሄደው 25ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በኋላ በነበሩ ስድስት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በብስክሌት ስፖርት አልተሳፈችም።
ዳግም በብስክሌት ስፖርት ወደ መድረኩ የተመለሰችው እ.አ.አ 2016 እና 2020 በሪዮ ዴጄኔሮና ቶኪዮ ከተሞች በተካሄዱት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነው።
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ ከሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11 2024 በፓሪስ ይካሄዳል።
በኦሊምፒኩ ውድድር ከሚካሄድባቸው 32 የስፖርት አይነቶች ብስክሌት ይገኝበታል።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ብስክሌተኞች በ2015 ዓ.ም በተለያዩ አገራት በተካሄዱ ሻምፒዮናዎች ላይ አመርቂ የሚባል ውጤት አስመዝግበዋል።
ፌዴሬሽኑ በቀጣዩ ኦሊምፒክ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ ተሳትፎ እንዲኖራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በመድረኩ መሳተፍ የምትችለው በተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በምታስመዘግበው ድምር ውጤት ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በጋና በተካሄደው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና እና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የብስክሌት ቅድመ ማጣሪያ በመሳተፍ አንድ ወርቅ እና ሁለት ነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በቀጣይም ኢትዮጵያ በሌሎች ውድድሮች ላይ እንደምትሳተፍና ፌዴሬሽኑም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ነው አቶ ሰለሞን የገለጹት።
በሌላ በኩል የብስክሌት ስፖርትን ለማሳደግ ፌደሬሽኑ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በተለይም ፌዴሬሽኑ ያለበትን የገንዘብ አቅም ውስንነት በመፍታት ገቢ ለማግኘት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተሞክሮዎችን እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ስፖርቱን ለማሳደግ መንግስት እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለብስክሌት ስፖርት ያላትን ምቹ የአየር ሁኔታ እና መልካም ምድር መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።