ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በየደረጃው ወጣት መሪዎችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ባህር ዳር መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በየደረጃው ወጣት መሪዎችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ ገለጹ።

"በወጣቶች አቅም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሃሳብ የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስልጠና በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ዶክተር ጋሻው አወቀ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ እንዳሉት ወጣቱ ለአገር ግንባታና ህብረ ብሄራዊ አንድነት የማይተካ ሚና አለው።

የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥም በየደረጃው የወጣት አደረጃጀቶችንና ወጣት መሪዎችን ማፍራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

አሁን ያለውን ተለዋዋጭ የአለም ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የአገርና ህዝብን አንድነት ማስጠበቅ ወቅቱ የሚጠይቀው ትግል መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

ለዚህም የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራሮችና አባላት የፓርቲውን ፕሮግራሞችና እሳቤዎች በአግባቡ ተረድተው የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ስልጠናው የሊጉ አመራሮችና አባላት የፓርቲውን መርሆዎች እንዲገነዘቡና የወጣቱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡበት አቅምና ክህሎት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።


 

የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ በአገሪቱ ባለፉት አራት ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ በብዙ ችግር ውስጥ ሆኖ በርካታ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልጿል።

ሊጉ የታዩ ችግሮችን በማረም ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አገራዊና አህጉራዊ አስተሳሰብን ለማዳበር ይሰራል ብሏል።

ስልጠናው በብልፅግና ፕሮግራሞች ላይ ግልፅነት ለመፍጠር፣ አለም አቀፍ ሁኔታውን ለመተንተንና ህብረ ብሄራዊነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም አስገንዝቧል።

ለስምንት ቀናት የሚቆየው ስልጠናው በብልፅግና መሰረታዊ አላማዎች፣ መርሆዎች፣ ፕሮግራሞችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

በተጨማሪም የሊጉን አመራሮችና አባላት በአመለካከት በማነፅ እንዲሁም እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማሳደግ በቀጣይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነም አብራርቷል።

በስልጠና ማስጀመሪያ መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር አለሙ ስሜን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና የሊግ አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም