ቀጥታ፡

አራተኛው ቀጣናዊ የፍልሰት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ)፦ አራተኛው ቀጣናዊ የፍልሰት ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ኢትዮጵያ ለዜጎች በአገር ውስጥ የስራ እድልን በመፍጠር ስደትን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባር አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እያጋጠሙ ያሉ የሰዎችን ስደት ለመከላከል ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች ገልጸዋል።


 

የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት(አይኤልኦ) የኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ ጂያን ዣኦ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባር ለመደገፍ በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ዛሬ መካሄድ የጀመረው የባለሙያዎች ውይይት ሲሆን ሙያተኞች የተወያዩባቸውን ጉዳዮች በጉባኤው ማጠቃለያ በሚካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የሚያቀርቡ ይሆናል።

በጉባኤው ላይ 11 የቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ እና አፍሪካ ቀንድ) አገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ለአራት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ የስራ ፈጠራና የሰዎች ፍልሰትን በፖሊሲ እና በሌሎች አማራጮች መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤውን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኤልኦ) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

ይውደዱ

አስተያየት

ያጋሩ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም