ቀጥታ፡

የጮቄ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም ልማት የ”ዓለም ድንቅ ቱሪዝም መንደር” ውድድር አሸናፊ  ሆነ 


አዲስ አበባ መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ)፦የዓለም ቱሪዝም ድርጅት(UNWTO) በጎጃም የሚገኘውን የጮቄ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም ልማት የ“ዓለም ድንቅ ቱሪዝም መንደር” (Best Tourism Village) ውድድር አሸናፊ አድርጎ መረጠ::


የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ከጮቄ ሙሉ ኢኮ ሎጅ ተወካዮች ጋር በመሆን ሽልማቱን  በሳውዲ አረቢያ አሉላ ከተማ  መቀበላቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ዋና ጸሐፊው በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ50 አገራት በላይ የሚገኙበት ከ100 የሚበልጡ የቱሪዝም መዳረሻዎች መሳተፋቸውን ገልጸው ማህበረሰቡን ያሳተፉ እና ዘላቂ ለሆኑት ሽልማት መበርከቱን ገልጸዋል።


 


በሽልማት መርሐ-ግብሩ ላይ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ መገኘታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።


በምሥራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ፣ ከባህር ወለል በላይ 4 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ ያለው እና ሰባት ሺህ ሄክታር ቦታን ይሸፍናል።


ከ270 በላይ ምንጮች እና ከ50 በላይ ለሚሆኑ ወንዞች ደግሞ መፍለቂያ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ታላቁ የ “ውሃ ማማ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡


ከጮቄ ተራራ ከሚፈልቁት 54 ወንዞች አብዛኛዎቹ የዓባይ ወንዝ ገባር ሲሆኑ ተራራው የበርካታ አገር በቀል ዛፎች እና ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ እጽዋት መብቀያ እንዲሁም የብዝሃ ሕይወት ማዕከል መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም