ቀጥታ፡

ተመራቂዎች በፈጠራና ቴክኖሎጂ ልማት በማተኮር የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግርን ማፋጠን አለባቸው - ዶክተር በለጠ ሞላ

 ባህር ዳር፣ ኢዜአ መጋቢት 03/2015 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በፈጠራና ቴክኖሎጂ ልማት በማተኮር የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግርን ማፋጠን አለባቸው ሲሉ  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ አስገነዘቡ። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በስራ ፈጠራ፣ ቢዝነስ ማመንጨትና ቴክኖሎጂ ልማት ለሰለጠኑ 50 ወጣቶች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ለማድረግ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡትን ትምህርት ተግባር ተኮር በማድረግ ተማሪዎችን በእውቀትና ክህሎት በማብቃት እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠን መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ሰሞኑን ለተከታታይ ሰባት ቀናት በባህር ዳር፣ ሃዋሳና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ለ150 ተመራቂዎች የስራ ፈጠራና ቢዝነስ ማመንጨት ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው፤ በቀጣይም ጅምሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ በማሪታይምና ሌሎች ተቋማት ለአገር እድገት መሰረት የሆኑ ሙያተኞች እያፈራ ይገኛል ብለዋል።


 

የልህቀት ማዕከል በመክፈት አጫጭር ስልጠና በመስጠት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን የማብቃትና የራሳቸውን ቢዝነስ እንዲጀምሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል። 

"ዩኒቨርሲቲው በጀት በመበጀት ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ነው" ያሉት ዶክተር ፍሬው የዛሬ ሰልጣኞችም ነገ ኢንዱስትሪያሊስት የመሆን አቅም እንዳላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አማረ ካሴ እንዳሉት፤ በዩኒቨርሲቲው ለ50 ተመራቂዎች የተሰጠው የአጭር ጊዜ ስልጠና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።

በቆይታቸውም ያላቸውን ሃሳብ በማመንጨት፣ አዋጭናቱና ተፈላጊነቱን በማረጋገጥ፣ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተፈላጊነት በማረጋገጥና ወደ ማመረት በመሸጋገር ራሳቸውንና አገራቸውን እንዴት መጥቀም እንደሚችሉ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም