ማዕከሉ የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ በማስፋፋት የሌማት ትሩፋት ግቦችን ለማሳካት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ በማስፋፋት የሌማት ትሩፋት ግቦችን ለማሳካት እየሰራ ነው

ሶዶ መጋቢት 3 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የሶዶ ዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ በማስፋፋት የተቀመጡ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ምህረቱ ማርቆስ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ "ጀርሲ" የተሰኙ የውጪ ዝርያ ያላቸውና የ"ቦረና" ላሞችን የማዳቀል ስራ እየሰራ ነው።
የተሻሻለ የወተት ዝርያ ያላቸው ጊደሮች በቀላሉ ማግኘት በእንስሳት አርቢው ዘንድ አዳጋች መሆኑን ጠቅሰው፣ ማዕከሉ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሌሎች ተቋማትና አርቢዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
ለአርሶ አደሮች ጊደሮችን ከማሰራጨት ባሻገር ለእንስሳት ልማት እንስቲትዩት፣ ለነቀምት አባላዘር ማምረቻ ማዕከል እና በክልሉ ለሚገኙ ሌሎች ማዕከላት የማሰራጨት ስራ በማከናወን ላይ መሆኑንምጠቁመዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ይህም እንደሀገር የተቀመጡ የሌማት ትሩፋት ግቦችን ለማሳካት መሠረት የሚጥል ነው።
ማዕከሉ ለዝርያ ማሻሻያ አገልገሎት የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶችን በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እያሰራጨ መሆኑንም አቶ ምህረቱ ተናግረዋል።
ለአብነት ባለፉት ስድስት ወራት ከእንስሳት ልማት እንስቲትዩት 11 ሺህ 500 ዶዝ ዘረመል (አባላዘር) በማምጣት ማሰራጨት መቻሉንም አስረድተዋል።
የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያና የመኖ ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ እያሱ ተረፈ በበኩላቸው የሶዶ ዳልጋ ከብት ማዕከሉ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን እንዲጠናክር የወተት ላሞች ዝሪያ ማሻሻል ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ የሚሰጠውን አገልግሎት በማጠናከር ከፍተኛ ወተት መስጠት የሚችሉ ዝሪያዎችን በማባዛት ከማሰራጨት ባለፈ የሀገረሰብ ዝርያዎችን የማዳቀል፣ የክትባትና ጤና አጠባበቅ እንዲሁም መኖ ልማት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዝርያ ማሻሻል ተግባር ባለፈ የመኖ ልማትና ጤና እንክብካቤ ወሳኝ መሆኑን አቶ እያሱ ገልጸው፤ እንስሳቱን በመከታተልና ክትባት በመስጠት በሽታን በመከላከል ለምርታማነት ዕድገት ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
በክልሉ የተሻሻለ ዝርያያላቸው ላሞችን የሚጠቀሙ በአማካይ ከ17 ሊትር በላይ ወተት እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ለማስፋት ማዕከሉን ለማጠናከር የተጀመረው ተግባር ለዘርፉ ስኬት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል ።