ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድቡ በትብብር ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ማሳየቱ ተገለጸ 

ሐረር፣ መጋቢት 3/2015 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በትብብር ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ማሳየቱን የታላቁ ህደሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

የህዳሴ ግድቡ ከተባበርን "ድህትን ማሸነፍ" እንደምንችል በተግባር ያሳየ ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ተካ ገለፁ፡፡ 

በሐረሪ ክልል  የታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ የማስተዋወቅ፣ ግንዛቤን መፍጠር እና ህዝባዊ ተሳትፎን የሚያጎለብት ሁለተኛው "የህዳሴ ጉዞ"  ንቅናቄ ተካሂዷል።

የንቅናቄ  መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ተካ ባስተላለፉት መልእክት ፕሮጀክቱ  መላው ኢትዮጵያውያን ብሄር፣ እምት እና የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው በአንድነት እና ወንድማማችነት መንፈስ በመረባረብ  እየገነቡት የሚገኝ ግድብ መሆኑንም  ገልፀዋል፡፡

ግድቡ ከተባበርን ድህነትን ማሸነፍ እንደምንችል በተግባር የታየበት ነው ብለዋል።


 

የሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን እና  የክልሉ የህዳሴ ግድብ ማስተባሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮዽያውያን ሃብት፣ ጉልበት እና እውቀት እየተገነባ የሚገኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮዽያውያን ከተባበሩ ድህንትን ብቻ ሳይን በሁሉም መስኮች ያሉ ችግሮችን የመፍታት ውስጣዊ አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።

በንቅናቄ መርሃግብሩ ላይ የ10 ሺህ ብር ቦንድ የገዙት አቶ ይትባረክ ተሰማ፤ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁንም የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠው፤ ኢትዮጵያውያን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱት ይህ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አመላክተዋል።

 የሀረር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ንግስት ኩምሳ በበኩላቸው በልጃቸው እና በራሳቸው ስም ቦንድ መግዛታቸውን በመጠቆም፤ የህዳሴ ግድቡ ከዳር እስኪደርስ ድጋፋቸውን አጠናከርረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡                                                       

በመርሃ ግብሩ ላይ በ8100 አጭር መልእክት ብሎም የቦንድ ሽያጭ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ጉዞ በአንድ ወር ውስጥ  በአገሪቱ በ200 ከተሞች ላይ እንደሚዘዋወር በእለቱ ተገልጿል።

 

 

 

 

 

 

  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

  

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም