ቀጥታ፡

የባህል ስፖርቶች ዉድድርና ፌስቲቫል ስኬታማ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ነው 

ሚዛን መጋቢት 3 / 2015 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አዘጋጅነት ሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ በነበረው 20ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ስኬታማ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

 ከየካቲት 26 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ በሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ የቆየው የባህል ስፖርቶቾ ዉድድርና ፌስቲቫል በአማራ ክልል የባህል ቡድን አጠቃላይ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቋል።

 በማጠቃለያ ስነ ስርአት ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳሉት የባህል ስፖርቶች ውድድር ሳምንት ኢትዮጵያ ከፍ ብላ የታየችበት ነው።

 "20ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 16ኛ የባህል ፌስቲቫል በባህል ዘርፍ ስኬታማ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ነው" ብለዋል።

 የውድድሩ ዋና ዓላማ በስፖርታዊ ውድድሩ ከማሸነፍ መሸነፍ ባለፈ ኢትዮጵያዊ የእርስ በእርስ ትስስር የሚጠናከርበት አጋጣሚ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

 "የባህል ስፖርቶች ውድድር እንደ ሀገር ጠንካራና ብቁ የባህል ስፖርተኞችን ለመለየት እና በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የባህል ስፖርቶች ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት ያለንን አቅም ለማወቅ ያስቻለ ነው" ብለዋል ።

 የባህል ስፖርቶች የሰላም ምልክቶች በመሆናቸው ሀገራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ሚኒስቴሩ ዘርፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

 በቂ ዝግጅት በማድረግ ውጤታማ ሀገር አቀፍ ውድድርና ፌስቲቫል እንዲደረግ ከፍተኛ አስተዋጾ ላበረከተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስጋና አቅርበዋል።


 

 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው "ከሁሉም ክልሎች የተገኙ የባህል ልዑካን ያሳዩት ጨዋነት እውነተኛ የኢትዮጵያን ማንነት ያጎላ ነው" ብለዋል።

 "እኛ አንድ ሆነን ስንቆም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች" ያሉት ኃላፊው "የባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ፌስቲቫሉ ሁሉም ብሔረሰቦች በአንድ ሆነው ባህላቸውን በማሳየት የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረጉበት ነው" ሲሉም አክለዋል ።

 20ኛውን የባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ፌስቲቫል የአማራ ክልል የባህል ቡድን በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ከሚኒስቴሩ የዋንጫ ሽልማት ተቀብሏል።

 የአማራ ክልል የባህል ቡድን መሪ አቶ አፈወርቅ ተፈራ ክልሉ የባህል ቡድኑ ባመጣው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

 "ከውድድር ባለፈ በርካታ የባህል ልምድ ልውውጥ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጋር አድርገናል" ያሉት አቶ አፈወርቅ ሀገራዊ ሰላምና አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ባህሎችን ለማልማት መስራት ይገባል" ብለዋል።

 አዘጋጁ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በስፖርታዊ ጨዋነት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ቀጣዩን 21ኛ የባህል ስፖርቶች ዉድድርና 17ኛውን የባህል ፌስቲቫል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚያዘጋጅ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም