የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2015/16 ምርት ዘመን 253 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማሰራጨት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2015/16 ምርት ዘመን 253 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማሰራጨት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 3/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2015/16 ምርት ዘመን 253 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮችና የግብርና ሥራ ለሚያከናውኑ ባለኃብቶች ለማሰራጨት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
በኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ በ26 የሰብል አይነቶች 69 የሚደርሱ ዝርያዎችን እያበዛ ነው።
ኮርፖሬሽኑ ዝርያዎቹን የሚያበዛው ተቋሙ በሚያስተዳድረው አምስት የምርጥ ዘር ማባዣ ማዕከላቶች፣ በተኮናተራቸው የእርሻ መሬቶችን እና በአርሶ አደር ማሳ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ይህንንም ተከትሎ በ2014/15 የምርት ዘመን በ15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘርን በማባዛት 300 ሺህ ኩንታል ለማምረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በእስካሁ ሂደትም 253 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መሰብሰቡን አስረድተዋል።
የተሰበሰበውን ምርጥ ዘር ለ2015/16 የምርት ዘመን ለአርሶ አደሮችና የግብርና ሥራ ለሚያከናውኑ ባለኃብቶች ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተሰበሰቡት ምርጥ ዘር ውስጥ የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ጎመን ዘር፣ ምስር፣ አኩሪ አተር፣ ባቄላ፣ ቦለቄ፣ ሽንብራና ተልባ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ምርጥ ዘሮቹ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ምርታማነትን የሚያሳደጉ፣ በሽታና አከባቢው ሁኔታን የሚቋቋሙ ከመሆናቸውም በላይ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከምርጥ ዘር አቅርቦት በተጨማሪ ለዘር አባዥ አርሶ አደሮች፣ ለግብርና ባለሞያዎችና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለኃብቶች ስለዘር አመራረት ቴክኖሎጂ ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በግብርናው ዘርፍ ከ30 እስከ 40 ዓመት ድረስ በተናጥል አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ አምስት ነባር ድርጅቶችን በማዋሀድ በ2008 ዓ.ም የተቋቋመ መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ነው።