ኅብረተሰቡ ለህዳሴው ግድብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኅብረተሰቡ ለህዳሴው ግድብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ድሬዳዋ መጋቢት 2/2015(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ኅብረተሰቡ ለፕሮጀክቱ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ ።
የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስና ህዝባዊ ድጋፍን ለማጠናከር ያለመ ህዝባዊ ንቅናቄ ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ዛሬ በተካሄደው ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ጉዞ ህዝባዊ ንቅናቄ በቦንድ ግዥና በሌሎች አማራጮች 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተሰብስቧል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገር ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በዚህ ጊዜ ገልጸዋል።
በዜጎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍና በጋለ ህዝባዊ ንቅናቄ እየተገባደደ የሚገኘውን የህዳሴ ግድብ በተጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ከፍታ ማረጋገጥ ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
በመላው አገሪቱ የተጀመረውን ህዝባዊ ንቅናቄ ከማጠናከር ባሻገር፤ በቦንድ ሽያጭና በ8100 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ዶክተር አረጋዊ አስታውቀዋል።
የግድቡን ግንባታ በሕዝባዊ ድጋፍ ጭምር ማጠናቀቅ የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዋን በላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገውም አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ተጀምሮ፤ በሰመራና በድሬዳዋ የቀጠለው ህዳሴ ግድብ ጉዞ ሕዝባዊ ንቅናቄ መላው አገሪቱን በማዳረስ እስከ 200 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የድሬዳዋ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዋቅጅራ በበኩላቸው ከአስተዳደሩ በዚህ ዓመት ለግድቡ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በተለያዩ አማራጮች ድጋፍ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው በዚሁ በሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ጉዞ ህዝባዊ ንቅናቄ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
ከአስተዳደሩ የግድቡ መሠረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከ92 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
በንቅናቄው የተሳተፉት የአስተዳደሩ ሠራተኞችና አመራሮች የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በቦንድ ግዢና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ተሳትፎቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የህዳሴው ግድብ ለአገር ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ እውን መሆን ወሳኝ ሚና ያበረክታል ያሉት ደግሞ ከድሬደዋ አስተዳደር አመራሮች መካከል ወይዘሮ ጫልቱ ሁሴን ናቸው።
በተለይ ድሬዳዋን የኢትዮጵያ የምስራቁ አካባቢ የኢንዱስትሪ ማዕከል በማድረግ ለዜጎች ሥራ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
ወይዘሮ ጫልቱ አክለውም "ዛሬ የ25 ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ፤ በቀጣይም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ እቀጥላለሁ፤ የፊታችን ማክሰኞ የምናከብረው የዓለም የሴቶች ቀን በዓል በቦንድ ግዢ ይደምቃል" ብለዋል።
ሌላው ለህዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ያደረጉት የመንግሥት ሠራተኛ አቶ ጁኔይዲን ኢብራሂም ግድቡ እስኪጠናቀቅ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም ቦንድ መግዛታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ።
በዚሁ ጊዜ ቦንድ የገዙት ነጋዴው አቶ አብዱረሒም ሱሌይማን በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ኤሌክትሪክ ማመንጨት መጀመር ለመላው ህዝብ ዕድገትና መለወጥ ወሳኝ በመሆኑ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ጉዞ ለአንድ ወር በመላው አገሪቱ እንደሚቀጥል በዚሁ ወቅት ተገልጿል።