የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦዲት ሪፖርት ያላቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ መጋቢት 16 እንዲያቀርቡ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦዲት ሪፖርት ያላቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ መጋቢት 16 እንዲያቀርቡ አሳሰበ
አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦዲት ሪፖርት ያላቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ መጋቢት 16 ድረስ ሒሳባቸውን በታወቀ የሒሳብ ባለሙያ በማስመርመር እንዲያቀርቡ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በበጀት እና ፋይናንስ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጥቂት ፓርቲዎች የ2014 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርታቸውን አላቀረቡም።
የ2015 ዓ.ም. በጀት ዘግይቶ የተመደበውም ፓርቲዎች የኦዲት ሪፖርታቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ባለማቅረባቸውና አሳማኝ ያልሆነ ሪፖርት ያቀረቡ እንዲያስተካክሉ በመመለሱ መሆኑን አክለዋል።
ምንም አይነት ሪፖርት ያላቀረቡ ፓርቲዎች የመጨረሻ የጊዜ ገደብ መጋቢት 16 ቀን 2015ዓ.ም ድረስ ብቻ መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።
እንዲሁም የወሰዱትን ድጋፍ ምንም ጥቅም ላይ ያላዋሉ ፓርቲዎች መኖራቸውን አያይዘው ገልጸዋል።
የ2014ዓ. ም. የኦዲት ሪፖርት ያላቀረቡ ፓርቲዎች በታወቀ የሒሳብ ባለሙያ የተረጋገጠ የኦዲት ሪፖርት እስካላቀረቡ ድረስ የ2015ዓ.ም በጀት ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ጠቁመዋል።
ለ2015 በጀት ዓመት ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ለመደበኛ በጀት መመደቡን ገልጸው፤ እንዲሁም ለፓርቲዎች ለሲቪክ ትምህርት የሚውል በጀት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የፓለቲካ ፓርቲዎች በጀቱ ቀደም ብሎ መሰጠት የነበረበት እና የዘገየ መሆኑን አንስተዋል።
በበጀት ድልድሉ ፓርቲዎች በአባልነት የያዟቸው የሴት አመራሮችና አባላት እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ቁጥር መታየት አለበት ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
ቦርዱ ፓርቲዎችን ለመደገፍ እየሄደበት ያለው ርቀት የሚያስመሰግነው መሆኑን ፓርቲዎቹ አንስተዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ የመዘግየቱ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዘገየውም ፓርቲዎች ካላቀረቧቸው የኦዲት ሪፖርት ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተዋል።
ፓርቲዎች በአባልነት ካቀረቧቸው የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄም ቦርዱ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።