የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን በማቋቋም አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው- አምባሳደር ጀማል በከር - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን በማቋቋም አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው- አምባሳደር ጀማል በከር
አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ) የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን በማቋቋም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ገለጹ።
ኢትዮጵያና ፓኪስታን በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነትና ጠንካራ ትብብር አላቸው።
ሁለቱ ሀገራት ይህን ጠንካራ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ የትብብር ማዕቀፎች ለመተግበር እየሰሩ ይገኛሉ።
በተለይ የሀገራቱ ሀገራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ቀጣናዊና ዘርፈ-ብዙ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ኢትዮጵያ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ከ7 ወራት በፊት ኤምባሲዋን ከፍታለች።
ይህን ተከትሎ ከሰሞኑ ከ80 በላይ የፓኪስታን ባለሀብቶችን ያቀፈ የንግድ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ተመልክቷል።
ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ምን አይነት የኢንቨስትመንት እድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ኢዜአ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ጋር ቆይታ አድርጓል።
አምባሳደር ጀማል የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በተለይ ከለውጡ ወዲህ በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።
በዚህም ፓኪስታን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ተፅዕኖዎችን በመቃወም አጋርነቷን ስታሳይ መቆየቷን አምባሳደር ጀማል ለአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በፓኪስታን በከፈተች በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን ካራቺ ከተማ በራራ እንዲጀምር መደረጉ የዲፕሎማሲ ስራው አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ የሚያደርገው በረራ በተለይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር እንዲሁም የቱሪዝም ፍሰቱን በማሳለጥ የዲፕሎማሲ ስራውን የበለጠ ለማጉላት እንደሚረዳም ገልጸዋል።
የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር የተናገሩት አምባሳደር ጀማል ባለሀብቶቹ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልፀዋል።
ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ኢንቨስትመንት ይዘው እንዲመጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ይህ በርካቶችን በስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ እድል መሆኑን አክለዋል።
በኢትዮጵያም ትልቅ የኢንዱስትሪ ዞን በማቋቋም የሲሚንቶ፣ የኬሚካል፣ የጨርቃጨርቅና ሌሎች ምርቶችን የማምረት ዕቅድ እንዳላቸው አብራርተዋል።
ፓኪስታን በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ከዚህ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ በማድረግ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ይህን እድል ለመጠቀም እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።