የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተቀበላቸውን 96 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተቀበላቸውን 96 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ አስመረቀ
ሶዶ መጋቢት 2/2015(ኢዜአ)፦ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ ክፍል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 96 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።ጨ
ምሩቃኑ ሲቪልና መካኒካል ምህንድስናን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው።
በምረቃ ሥነ-ስርአቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ እንዳሉት፣ በሀገሪቱ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን የተጀመረው ጥረት ከዳር እንዲደርስ ዜጎች አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል።
ሙስናን ጨምሮ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ከሚያስከትሉ ተግባራት በመቆጠብ ለሀገር ልማት በጋራ መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ እንድትል ከሚያደርጉ ልማቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ሁሉም የልማት ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ እጅ ለእጅ ተያይዞ የመስራትን አስፈላጊነትም አስረድተዋል።
በሰሜኑ ክፍል የነበረው የጸጥታ ችግር ተፈትቶ አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም በማጽናት ልማትን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረትም ምሩቃን የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ከምሩቃን መካከል በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 94 ውጤት በማስመዝገብ የእለቱ ተሸላሚ የሆነችው ትህትና ባይሳ በበኩሏ፣ የነበረው የሰላም እጦቱ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግራለች።
"መንግስትና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተስፋችን እንዲለመልም አድርገዋል፤ በዚህም አመስግናለሁ" ያለችው ተመራቂዋ፣ ያለ ሰላም ምንም ማድረግ እንደማይቻል ገልጻለች።
በዩኒቨርሲቲ ቆይተዋ የሰላም ዋጋው የማይተመን መሆኑን መረዳቷን ተናግራ፣ በቀጣይ በምትንቀሳቀስበት ሁሉ ለሀገር ሰላም መጠናከር የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች።
ልጃቸውን ለማስመረቅ የመጡት ወይዘሮ አበበች ቀጥይበሉ በሰጡት አስተያየት የጸጥታ ችግር በነበረበት ወቅት አክሱም ዩኒቨርሲቲ ለነበረው ልጃቸው ሲጨነቁ ጤናቸው ተቃውሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
የጭንቅ ጊዜው አልፎ ልጃቸው ትምህርቱን አጠናቆ ዛሬ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የልጃቸው ትምህርት ተቋርጦ እንዳይቀር መንግስትና ዩኒቨርሲቲው ላደረጉት እገዛም አመስግነዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላት፣የወላይታ ሶዶ ዞን አስተዳደር ሃላፊዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።